ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሰሜን አየርላንድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ዘረኛነትን በመቃወም ሰልፍ አካሄዱ
በሰሜን አየርላንድ ቤልፋስት ከተማ ዘረኛነትን በመቃወም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ ወጥተዋል።
ባለፈው ሳምንት ቤልፋስት ከተማ በስለት የተፈጸመን ጥቃት ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ ሰዎች መኖሪያ ቤታቸውን ለቅቀው ለመውጣት መገደዳቸው ይታወሳል።
ትናንት ቅዳሜ በከተማዋ የፀረ ዘረኛነት ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
የስለት ጥቃቱን ተከትሎ ቤቶች እና መኪኞች ሲቃጠሉ የሕዝብ ትራንስፖርትም ተቋርጧል።
በስለት ጥቃት በመፈጸም የተጠረጠረው የ30 ዓመት ሱዳናዊ ፍርድ ቤት ቀርቦ የግድያ ሙከራ ክስ ቀርቦበታል።
'ቱጌዘር አጌንስት ሄት' በተባለ ንቅናቄ አማካኝነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቤልፋስት ማዘጋጃ ቤት ተሰባስበዋል። ፖሊስ ሰልፈኞቹን ለማስተናገድ አውራ ጎዳናዎችን ዘግቷል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሠራተኞች ማኅበራት በሰልፉ ተገኝተዋል።
'ዘረኛነትን ተዋጉ' 'ስደተኞች እንኳን ደኅና መጣችሁ' 'ነውጥ ቤልፋስንት አይወክልም' የሚሉና ሌሎችም መፈክሮች ታይተዋል።
የዩናይትድ አጌንስት ሬሲዝም ቃል አቀባይ ኢቫንካ አንቶቫ "በዚህ ሳምንት ፈጽሞ የማይረሳ ነገር አይተናል። ልጆች እና ቤተሰቦች በፍርሃት ከቤታቸው ሸሽተዋል። ሃብታሞች እና ኃያላን እንዴት ድረ ገጾችን መጠቀሚያ እንዳደረጉም ተመልክተናል" ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት በቤልፋስት የስለት ጥቃት ለደረሰበት ግለሰብ ሐዘኔታቸውን ገልጸዋል።
የ40 ዓመቱ ግለሰብ በዐይኑ እና አንገቱ ላይ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት እና በሆስፒታል ሕክምና እየተከታተለ እንደሆነ ተገልጿል።
የስለት ጥቃቱን ተከትሎ በከተማዋ ነውጥ መነሳቱን በመጥቀስ "መላው ዓለም ቤልፋስትን በስጋት ሲመለከት ነበር" ብለዋል።
"ለዘረኛነት ምክንያት የለውም። በከተማችን ዘረኛነት ቦታም አይሰጠውም።"
የከተማዋ ነዋሪዎች ለቅቀው እንዲወጡ እና ምግብ እንዲያገኙ ድጋፍ ለሰጡ ሰዎች ምስጋና አቅርበዋል። በፍርሃት የተሸበቡ ማኅበረሰቦችን በማበረታታትም ብዙዎች እገዛ አድርገዋል።
ቃል አቀባዩዋ እንደተናገሩት የመንግሥት ባለሥልጣናት ለሰልፉ ድጋፍ ለማድረግ ጥያቄ አቅርበዋል።
"ዘረኛነትን ለመታገል ገንዘብ መመደብ አለባቸው። ቀኝ ዘመሞች ደግሞ ከማኅበረሰባችን እንዲወጡ መልዕክት እናስተላልፋለን። መከፋፈል በቅቶናል፤ ዘረኛነትን አንታገስም" ብለዋል።
የስደተኞች ትግል እና የሠራተኞች ትግል ተመሳሳይ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ባለፈው ሳምንት የሰሜን አየርላንድ ፖሊስ ጥቃቱን ተከትሎ "በውስን አካባቢዎች የተፈጠረው ነውጥ" እንዲረጋጋ ጠይቋል።
ጥቃቱን በመቃወም በለንደንዴሪ፣ አንትሪም፣ ኒውታውንአቤይ፣ ባሌሜና፣ ባንጎር እና ቤልፋስት የሚገኙ ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተዋል።
በርካታ የሕዝብ እንደራሴዎች ፖሊስ ለስደተኛ ሴቶች ከለላ አልሰጠም ብለው ወቅሰዋል። ስደተኞች የጥቃት እና ዛቻ ዒላማ መደረጋቸውን አውግዘዋል።
እስካሁን ድረስ ፖሊስ 23 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል። 17 ሰዎች በፍርድ ቤት ክስ ቀርቦባቸዋል።
የንቅናቄ ቡድን የሆነው 'ውሜን ሪሶርስ ኤንድ ዲቨሎፕመንት ኤጀንሲ' ውስጥ የሚሠሩት ኤሌን ኮሪ "ነውጡ ሴቶች እና ታዳጊዎችን ለአደጋ ያጋለጠ ነው" ብለዋል።
ነውጡ በርካቶችን "እንዳስቀየመ እና እንዳስቆጣም" ገልጸዋል።
በቤልፈስት ለ20 ዓመታት የኖረው መሐመድ ኢልታይብ ቁጣን "በትክክለኛው መንገድ ለመግለጽ" ሁከት እንደማያስፈልግ ተናግሯል።
በከተማዋ የተነሳውን ሁከት በመቃወም የፀረ ዘረኛነት ሰልፍ መካሄዱ የተሻለ ስሜት እንደፈጠረለትም ገልጿል።
ሰልፉን የታደመችው ማናል መሐዲ በሰልፉ ምክንያት የምትፈልገውን ማረጋገጫ እንዳገኘች እና ማኅበረሰቡ "ገፍቶናል" የሚለው ስሜቷ እንደጠፋ ተናግራለች።