በአፍጋኒስታን በቪዛ ፈላጊዎች መካከል በተፈጠረ መረጋገጥ 11 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአፍጋኒስታን አንድ ስታዲየም ውስጥ የፓኪስታን ቪዛ ለማግኘት በርካታ ሰዎች መሰባሰባቸውን ተከትሎ በተፈጠረ መገፋፋት 11 ሴቶች ተረጋግጠው ሲሞቱ ብዙዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ባለስልጣናት አስታወቁ።
አደጋው ሊከሰት የቻለው በሺዎች የሚቆጠሩ አፍጋኒስታናውያን ወደ ፓኪስታን የሚያስገባቸውን ቪዛ ለማግኘት መሰብሰባቸውን ተከትሎ እንደሆነ የአካባቢው ቃል አቀባይ ገልጸዋል።
በአፍጋኒስታኗ ጃላላባድ ከተማ የሚገኘው የቪዛ ማዕከል ሰዎቹን ማስተናገድ እንደማይችል በመገመቱ ነበር በሺዎች የሚቆጠሩት ሰዎች ወደ ስታዲየሙ ሄደው አገልግሎቱን እንዲያገኙ የተደረገው።
በኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለሰባት ወራት ተቋርጦ የነበረው የፓኪስታን ቪዛ አገልለግሎት በድጋሚ መሰጠት የተጀመረው በቅርቡ ነው።
''ቪዛ ጠያቂዎቹ ከኃላፊዎች ሕጋዊ ወረቀት ለማግኘት ከፍተኛ ግፊያ ያደርጉ ነበር። ነገር ግን በድንገት ሕዝቡ ከቁጥጥር ውጪ ሆነ፤ ሰዎችም በሰዎች ላይ መረማመድና መገፋፋት ጀመሩ'' ብለዋል አንድ የከተማይቱ ኃላፊ ለሬውተርስ የዜና ወኪል ሲናገሩ።
በአፍጋኒስታን ፓኪስታን አምባሳደር የሆኑት ማንሱር አህመድ ክሃን በበኩላቸው በተፈጠረው አደጋ በእጅጉ ማዘናቸውን በመግለጽ አገራቸው የቪዛ ሰአጣጥ ስርአቱን ለማሻሻልና ፈጣን ለማድረግ ከአፍጋኒስታን ጋር እየሰራች እንደሆነ ገልጸዋል።
በአፍጋኒስታን የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ወንዶችና ሴቶች አንድ ላይ መሰለፍ የማይችሉ ሲሆን ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል በርካታዎቹ ሴቶችና እድሜያቸው የገፋ ሰዎች እንደሆኑ ተገልጿል።
በርካታ አፍጋኒስታናውያን ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ፣ የተሻለ ሕክምና ለማግኘት፣ ስራ ፍለጋ አልያም በአገራቸው ያለውን ጦርነት ለማምለጥ በማሰብ ወደ ጎረቤት አገር ፓኪስታን ለመግባት ጥረት ያደርጋሉ።












