ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እግር ኳስ፡የቀድሞው የጋና እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዚደንት የታጣለባቸው የሕይወት ዘመን እግድ ተቀነሰላቸው
የቀድሞው የጋና እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዚደንት ክዌሲ ንያንታኪ የተጣለባቸው የሕይወት ዘመን እገዳ ወደ 15 ዓመት ዝቅ እንደተደረገላቸው ተገለፀ።
ይህ የሆነው በስፖርት የግልግል ዳኝነት ተቋም [ካስ] ይግባኝ ከጠየቁ በኋላ ነው።
ይህንንም ተከትሎም " ክዌሴ ንያንታኪ በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍም ደረጃ ከእግር ኳስ ጋር ከተገናኙ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ከጥቅምት 29/ 2018 ጀምሮ ለ15 ዓመታት ታግደዋል" ሲል የግልግል ተቋሙ ለቢቢሲ አስታውቋል።
የቀድሞው የእግር ኳስ ፌደሬሽን ምክር ቤት አባል እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ምክትል ፕሬዚደንት ክዌሴ፤ ጉቦ በመቀበልና በሙስና ቅሌት ሳቢያ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽን (ፊፋ) ለሕይወት ዘመን የታገዱት እአአ.ጥቅምት 2018 ነበር።
ካስ ሚያዚያ ወር ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎም የስዊዝ ፍርድ ቤት ጋናዊው ላይ መጀመሪያ ላይ ጥሎት የነበረው የ550 ሺህ ዶላር ቅጣትም ወደ 110 ሺህ ዝቅ ተደርጎላቸዋል።
የፊፋ የሥነምግባር ኮሚቴ ውሳኔ ካሰለፈባቸው ከቀናት በኋላ ስማቸውን እንደገና ለማደስ ፍላጎት እንዳላቸው የገለፁት ክዌሴ፤ ታህሳስ 2018 ላይ ለግልግል ተቋሙ (ካስ) ይግባኝ ብለው ነበር።
ክዌሲ ራሱን በደበቀ የምርመራ ጋዜጠኛ 65 ሺህ ዶላር ጉቦ ሲቀበሉ በድብቅ ተቀርፀው ነበር።
65 ሺህ ዶላር ጉቦ ሲቀበሉ የሚያሳየው ፊልም በጋና የምርመራ ጋዜጠኛ አናስ አረሜያው ነበር የተቀረፀው።
ፊልሙ ክዌሴ በጋና እግር ኳስ ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ የፈለገ ባለሃብት መስሎ ከቀረባቸው ጋዜጠኛ ገንዘቡን ተቀብለው ፌስታል ውስጥ ሲከቱት ያሳያል።
ከዚያም በኋላ ሚሊየን ዶላሮችን ሊያስገኝ ይችል የነበረና እአአ. ከ2005 ጀምሮ ለመሩት ለጋና እግር ኳስ ማህበር የተወሰነ ድጋፍ ( ስፖንሰርሽፕ) ወደ ራሳቸው ድርጅቶች እንዲዛወሩ ስምምነት አድርገዋል።
የቢቢሲ የምርመራ ክፍል 'አፍሪካ አይ' ፊልሙን አስተላልፎት ነበር።
ይህ በምዕራብ አፍሪካ እና ኬንያ ከመቶ በላይ የሚሆኑ የእግር ኳስ ኃላፊዎች ከጨዋታ በፊት ገንዘብ ሲቀበሉ የሚያሳየው የምርመራ ዘገባ በቢቢሲ ከተላለፈ በኋላም ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ዘገባው የአፍሪካ እግር ኳስ ማነቆዎችን በግልጽ ያሳየ ነውም ተብሏል።
ሁለት አመት የፈጀው እና ለብዙ ሰአታት የተቀረጸው ተንቀሳቃሽ ምስል የእግር ኳስ ዳኞች እና ኃላፊዎች ጨዋታዎች ከመካሄዳቸው በፊት ገንዘብ ሲቀበሉ ያሳያል።
ክዌሲ በወቅቱ ፊልሙ እርሳቸውን በሃሰት ለመወንጀል የተሰራ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተው ነበር ።
ፊልሙ በዚያው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ለሕዝብ ዕይታ ከበቃ በኋላ በአፍሪካ እግር ኳስ ሁለተኛው ተፅእኖ ፈጣሪ ሰው ከጋና እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዚደንትነት ለቀዋል።