ኢትዮጵያ፡ በምስራቅ አፍሪካ በጎርፍ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ስድስት እጥፍ መጨመሩ ተገለፀ

ሱዳን ያጋጠማት ጎርፍ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

በምስራቅ አፍሪካ በጎርፍ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር በስድስት እጥፍ መጨመሩን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።

ሪፖርቱ የአምስት አመታትን መረጃም ያጠናቀረ ነው።

በዘንድሮው ጎርፍ ስድስት ሚሊዮን ሰዎች የተጠቁ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል 1.5 ሚሊዮን ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

በቀጠናው የሚገኙ አንዳንድ አገራትም በክፍለ ዘመኑ አጋጥሞ የማያውቅ ከፍተኛ ዝናብና ጎርፍ እንዳጋጠማቸውም ተዘግቧል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ በጎርፉ ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ድንገተኛ እርዳታ እያደረገም ይገኛል።

በቀጠናውም ላይ ያጋጠመው ጉዳት አስከፊነት የተባበሩት መንግሥታትን አስጊ ነው ብሎታል።

በጎሮጎሳውያኑ 2016 ከሚሊዮን ሰዎች በላይ በጎርፍ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ይህ ቁጥርም በ2019 ወደ አራት ሚሊዮን አሻቅቧል።

በተለይም በአንዳንድ አካባቢዎች በህዳር ላይ የሚጠበቀው ዝናብ የበለጠ ጉዳት ያስከትላልም ተብሏል።

ከሐምሌ ጀምሮ በሱዳን ከፍተኛ ጎርፍ የተከሰተ ሲሆን በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳንም እንዲሁ ጎርፍ ሚሊዮኖችን ቤትና ንብረት አልባ አድርጓቸዋል።

የህንድ ውቅያኖስ በከፍተኛ ሁኔታ መሞቅ ለከፍተኛ ዝናቡ ምክንያት እንደሆነ ሳይንቲስቶችም ገልፀዋል።