ኮቪድ-19፡ በስህተት የ16 ሺህ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ውጤት ሳይገለጽ ቀረ

የፊት ጭምብል ያደረገ የፓርኪንግ ሰራተኛ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

ታትሟል

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በገጠመ የቴክኒክ ስህተት ወደ 16 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ሳይገለጽ ቀረ። ይህም በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ለመለየት የሚደረገውን ጥረት አጓቷል።

የአገሪቱ የሕብረተሰብ ጤና ተቋም እንዳለው ከመስከረም 25 እስከ ጥቅምት 2 ድረስ 15,841 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው በእለታዊ ሪፖርት ሳይካተት ቀርቷል።

ሪፖርት ያልተደረጉት ሰዎች ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ በወጡት እለታዊ ሪፖርቶች ተካተዋል።

ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ውጤታቸው ቢነገራቸውም ከእነሱ ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች መረጃው እንዳልደረሳቸው ተቋሙ አስታውቋል።

በገጠመው የቴክኒክ ስህተት ምክንያት ባለፈው ሳምንት የወጡ ሪፖርቶች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን አሳንሰዋል።

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በቫይረሱ እንደተያዙ የተገለጸው 7,000 ሰዎች ቢሆንም፤ ትክክለኛው ቁጥር ወደ 11,000 ይጠጋል።

ሪፖርት ካልተደረጉት ሰዎች አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት የሰሜን ምዕራብ ኢንግላንድ ነዋሪዎች ናቸው።

በርካታ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የሚኖሩት በሊቨርፑል እና በማንችስተር ነው።

ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች በአጠቃላይ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።

የክትባት ምርምር ግብረ ኃይል ኃላፊ ኬት ቢንግሀም ለፋይናንሽያል ታይምስ እንደተናገሩት፤ ከዩኬ ዜጎች ከፊሉ ይከተባሉ።

“ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ሰዎች ክትባት አይሰጥም። ክትባቱ ከ50 ዓመት በላይ ለሆኑና በዋናነትም ለጤና ባለሙያዎችና አረጋውያንን ለሚንከባከቡ ሰዎች ይሰጣል” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ወረርሽኙን የማሸነፍ ተስፋ እንዳለ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ማኅበረሰቡ “ጥንቃቄ ማድረግ እንጂ መፍራት የለበትም” ሲሉም አክለዋል።

በአገሪቱ የምርመራ ውጤት መዘግየቱ መንግሥትን እያስተቸ ባለበት ወቅት፤ በስህተት ውጤታቸው ያልተገለጸ ሰዎች የመኖራቸው ዜና ነገሮችን አባብሷል።

በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች መረጃውን አለማግኘታቸው ሌላው አሳሳቢ ነገር ነው። ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ቫይረሱ ከተገኘበት ሰው ጋር ንክኪ የነበራቸው ግለሰቦች በ48 ሰዓታት ውስጥ ሊነገራቸው ይገባል።

ስህተቱ የኮምፒውተር እንደሆነና አሁን መስተካከሉ ተገልጿል።

መንግሥት ትላንት ባወጣው ሪፖርት ተጨማሪ 22,961 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸውና አጠቃላይ በበሽታው የተያዙ ቁጥር 502,978 መድረሱን ገልጿል።

የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ኃላፊው ማይክል ብሮይድ እንዳሉት፤ አብዛኞቹ ሪፖርት ያልተደረጉ ቁጥሮች የቅርብ ጊዜ የምርመራ ውጤት ናቸው።

“ችግሩን በአፋጣኝ ለመቅረፍና የምርመራ ውጤቶቹን ለመግለጽ ሞክረናል። ስህተቱ ሊፈጥር የሚችለውን ስጋት እንረዳለን። በቀጣይ ተመሳሳይ ነገር እንዳይፈጠር ጥብቅ እርምጃ ወስደናል” ብለዋል።

ኮሮና
Banner