ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አውስትራሊያ: በታስሜኒያ መውጫ አጥተው በአንድ ስፍራ ከተቀረቀሩ አሳ ነባሪዎች መካከል 90ዎቹ ሞቱ
በአውስትራሊያዋ ታስሜኒያ የባህር ዳርቻ ከተቀረቀሩ 270 አሳ ነባሪዎች መካከል 90ዎቹ መሞታቸው ሲገለፅ የሟቾቹ ቁጥር ይጨምራል ተብሎ ተሰግቷል።
በአገሪቱ ምዕራብ አቅጣጫ በሚገኘው የባህር ዳርቻ አሳ ነባሪዎቹ በአንድ ስፍራ ተቀርቅረው የታዩት ትናንት ነበር።
የውሃ ውስጥ ስነ ህይወት ተመራማሪዎች ቀናትን ይፈጃል ብለው በገመቱት የነፍስ አድን ስራ ተጠምደዋል።
አሳ ነባሪዎቹን ወደ ውቅያኖሱ ዳርቻ ምን እንደ ገፋቸው የታወቀ ነገር የለም። በአካባቢው በውቅያኖሱ ዳር አሳነባሪዎችን ማየት የተለመደ ሲሆን ለአስርታት በዚህ መጠን ታይተው አያውቁም።
ታስሜኒያ እኤአ በ2009 ዓ.ም 200 አሳነባሪዎች በባህር ዳርቻዋ ላይ ተቀርቅረው መውጫ ጠፍቷቸው ተመልክታ ታውቃለች።
የታስሜኒያ የውሃ ውስጥ ህይወትን ለመንከባከብና ለመጠበቅ የተቋቋመው ፕሮግራም አባላት ሰኞ እለት ረፋድ ላይ ነበር አሳ ነባሪዎቹ መቀርቀራቸውንና መውጫ እንደጠፋቸው የሰሙት።
አሳነባሪዎቹ የተቀረቀሩበት ስፍራ ከእይታ የተገለለ ደሴት አቅራብያ ሲሆን ለመኪና የሚሆን መንገድ እንዲሁም ጀልባና መርከቦችን ለማሰማራት አስቸጋሪ ቦታ ነው ተብሏል።
በርካቶቹ አሳ ነባሪዎች "በአንጻራዊነት ለመድረስ አስቸጋሪ" በሆነ ስፍራ ተቀርቅረዋል ሲሉ የነፍስ አድን ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።
40 አባላት ያሉት የነፍስ አድን ባለሙያዎች ቡድን ከማክሰኞ ማለዳ ጀምሮ በመሳሪያ በመታገዝ የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን አሳ ነባሪዎች "ዳግም ወደ ውቅያኖሱ እንዲቀዝፉ" ረድቷቸዋል።
ወደ ባህር ዳርቻው ተጠግተው መቅዘፍ የተቸገሩት አሳነባሪዎችን ህይወት ማትረፍ ከባድ እንደሚሆን የሚናገሩት ባለሙያዎች፣ በከፊል በውሃ ውስጥ ሆነው መንቀሳቀስ ያልቻሉትን ግን ዳግም ወደ ትልቁ የውቅያኖስ ክፍል እንዲቀዝፉ መርዳት አስቸጋሪ እንደማይሆን ተናግረዋል።
አሳ ነባሪዎቹ በውሃ ውስጥ ሆነው በጥሩ ጤንነት ላይ ከሆኑ ቀጥሎ ያለው ስራ እምብዛም አስጨናቂ እንደማይሆን ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።
የነፍስ አድን ባለሙያዎች አባል የሆኑት ዶ/ር ካርሊዮን ስራቸውን ከባድ የሚያደርገው የውቅያኖሱ ወጀብ መሆኑን ይናገራሉ። ስራቸውን ለማቀላጠፍም ጀልባ እንደሚጠቀሙ ጨምረው አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ በርካቶቹ አሳ ነባሪዎቹ ለሰውም ለመሳሪያውም የከበዱ ግዙፎች እንዲሁም ለመንቀሳቀስ ምቹ ስፍራ ላይ አይደሉም። እነዚህ የአሳ ነባሪ ዝርያዎች ፓይለት የሚባሉ ሲሆን እስከ ሰባት ሜትር ድረስ ርዝማኔ እነንዲሁም እስከ ሶስት ቶን ድረስ ክብደት አላቸው።
እነዚህ የነፍስ አደን ሰራተኞች ከዚህ በፊት ካላቸው ልምድ ፓይለት አሳ ነባሪዎች በእንዲህ አይነት ስፍራ ሶስትና አራት ቀን በሕይወት ሊቆዩ እንደሚችሉ ያውቃሉ። እንዲሁም ደግሞ አብዛኛዎቹ "በጥሩ ሁኔታ በውሃ ውስጥ ይገኛሉ" ብለዋል ዶ/ር ካርሊዮን።
ተመራማሪዎች አሳ ነባሪዎች ስለምን በእንዲህ አይነት ስፍራ ቀዝፈው በመውጣት እንደሚቀረቀሩ እስካሁን ድረስ አልደረሱበትም።
በአውስትራሊያና በኒውዚላንድ የተለያዩ የውቅያኖስ ክፍል እስከ 1000 የሚጠጉ አሳነባሪዎች በጋራ በመሆን ከቦታ ቦታ ይሰደዳሉ።
ተመራማሪዎች እንደሚሉት አሳ ነባሪዎቹ የሚከተሉት መሪ ሲኖራቸው፣ ያላቸው ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር በአንድ ላይ በመሆን እንዲህ አይነት ስፍራ እንዲቀረቀሩ ያደርጋቸዋል።
በኒውዚላንድ በ2018 ዓ.ም ከ200 በላይ ፓይለት አሳነባሪዎች በሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዲህ ባለ አጣብቂኝ ስፍራ ተቀርቅረው መውጫ በማጣት ሞተዋል።