በኢትዮጵያ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ተገለፀ

ታትሟል

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አስታወቀ።

በያዝነው ወር የወጣውና ከኢትዮጵያ መንግሥትም እውቅና እንደተሰጠው በተገለጸው የድርጅቱ ሪፖርት መነሻ ያደረገው ከሰኔ እስከ ሐምሌ የተሰበሰበ መረጃን ነው።

መረጃው የተገኘው ከ1200 የተፈናቃዮች መጠለያዎች እንዲሁም ከሌላ 1200 ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች የተመለሱባቸው መንደሮች ነው።

ሰዎች በዋነኛነት እየተፈናቀሉ የሚገኙት በግጭት ሳቢያ ሲሆን፤ በመላው አገሪቱ 1,233,557 ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ።

ሁለተኛው ምክንያት ድርቅ ሲሆን 351 ሺህ 62 ሰዎችን አፈናቅሏል። በጎርፍ ሳቢያ የተፈናቀሉ ደግሞ 104 ሺህ 696 ናቸው።

ድርጅቱ በደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች በሰበሰበው መረጃ መሠረት፤ ባጠቃላይ 93 ሺህ 982 ተፈናቅለዋል።

66,994ሰዎች (71 በመቶ ያህሉ) የተፈናቀሉት በግጭት ምክንያት ሲሆን፤ 26,988ሰዎች (29 በመቶው) በጎርፍ ሳቢያ ቤት ንብረታቸውን አጥተዋል።

ከደህንንት፣ የመሠረተ ልማት ውስንነት እና የአየር ንብረት ለውጥ አንጻር በተለያዩ ክልሎች የተሠራው ዳሰሳ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚለያይ ነው። ሆኖም ግን በሁሉም ክልሎች በመዘዋወር መረጃ ተጠናቅሯል።

የድርጅቱ ሪፖርት ተፈናቃዮች አሁን ከሚገኙባቸው መጠለያዎችና በተለያየ ጊዜ የተፈናቀሉ ሰዎች በመልሶ ማቋቋም ከሚኖሩባቸው መንደሮች የተሰባሰበ ነው።

መልሶ ማቋቋሚያ ሂደትን በተመለከተ ምን ያህል የመሠረተ ልማት አቅርቦት አለ? ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው ለመመለስ የሚደረገው ጥረትስ ምን ይመስላል? የሚለው ተፈትሿል።

መንግሥት ካለፈው ዓመት ግንቦት አንስቶ ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራ ጀምሯል። አምና ሚያዝያ ላይ የተፈናቃዮች ቁጥር 3.04 ሚሊዮን ደርሶ ነበር።

በአገሪቱ ባጠቃላይ1,400,892 ተፈናቃዮች ወደ መንደራቸው ተመልሰዋል።

ከተመላሾች መካከል 1,328,652 (95 በመቶ ገደማው) በግጭት ምክንያት ነበር የተፈናቀሉት።

ድርጅቱ ከጎርጎሮሳውያኑ 2016 ጀምሮ በተፈናቃዮች መጠለያዎች፣ ከ2019 ወዲህ ደግሞ ተመላሾች በሚኖሩባቸው መንደሮች ዳሰሳ ያካሂዳል።

የድርጅቱ የኢትዮጵያ ጊዜያዊ አስተባባሪ ሳራ ቾንግ “ተፈናቃዮችና ተመላሾችን በተመለከተ ጥልቅና አስተማማኝ መረጃ በመስጠት እንቀጥላለን” ብለዋል።

መረጃው ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረግና ፖሊሲ ለመቅረጽ ይውላል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም አክለዋል።

በድርጅቱ የሚወጡ ሪፖርቶች በአገራዊ ደረጃ እንዲሁም በቀጠናውም የሰዎችን እንቅስቃሴ ለመቃኘት ይረዳሉ።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ከአገራዊው አደጋ መከላከልና ዝግጁነት እንዲሁም ከሠራተኞችና ማኅበራዊ ጉዳይ ጋር በቅርበት ይሠራል።

መረጃው ከመንግሥት በተጨማሪ ለኢ-መንግሥታዊ ድጋፍ አድራጊዎችና የመብት ተሟጋቾችም ይሰጣል።