ኡጋንዳና ታንዛኒያ በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁን የነዳጅ መስመር ዝርጋታ ስምምነት አደረጉ

ታትሟል

ጎረቤታሞቹ ኡጋንዳና ታንዛኒያ ግዙፍ ስምምነት አድርገዋል፡፡

ስምምነቱ ድፍድፍ ነዳጅ ማስተላለፍያ መስመር ዝርጋታን የተመለከተ ነው፡፡ ይህ 1445 ኪሎ ሜትር የሚደርሰው የነዳጅ ማስተላለፍያ ትቦ ከኡጋንዳ የነዳጅ ማውጫ ተነስቶ ታንጋ ወደብ የሚዘልቅ ይሆናል፡፡ ታንጋ ወደብ የታንዛኒያ የገቢ-ወጪ ወደቧ ነው፡፡

የዚህ ግዙፍ ቧንቧ ጠቅላላ የግንባታው ወጪ ከ3 ቢሊዮን ተኩል ያልፋል ነው የተባለው፡፡ በዚህ ግዙፍ የሁለቱ አገራት ስምምነት ጆን ማጉፉሊና ዩዌሪ ሙሴቬኒ ተገኝተዋል፡፡በኡጋንዳ ነዳጅ ተገኘ የተባለው በፈረንጆቹ በ2006 ነበር፡፡

ነገር ግን ነዳጅ የማውጣቱ ተግባር እጅግ ሊዘገይ የቻለው መሠረተ ልማት ባለመሟላቱ ነበር፡፡ ለምሳሌ ነዳጁን አውጥቶ ወደ ወደብ የሚያደርስ ቧንቧ ዝርጋታ አልተካሄደም ነበር፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁ የነዳጅ መስመር ዝርጋታ ይሆናል የተባለለት ይህ ግንባታ መቼ በትክክል እንደሚጀመር ቁርጥ ቀን አልተቆረጠም፡፡ሆኖም የነዳጅ መስመሩ ሲዘረጋ ለተወሰኑ የኡጋንዳ ማኅበረሰብ አባላት ትልቅ ስጋት ይደቅናል የሚል ፍርሃት መኖሩ ከወዲሁ ተሰምቷል፡፡

ግንባታው በትንሹ 12ሺ ቤተሰቦችን ከመሬታቸው ያፈናቅላል፤ ገቢያቸውን ያናጋልም ተብሏል፡፡ ይህን ያሉት ኦክስፋምና የኢንተርናሽናል ፌዴሬሽን ለሰብአዊ መብት የተሰኙ ግብረሰናይ ድርጅቶች ናቸው፡፡

ግንባታውን የሚያካሄዱት የፈረንሳዩ ቶታል ከቻይናው ሲኤን ኦኦ ሲ ጋር በመሆን ነው፡፡ የእሁዱ የፊርማ ሥነ ሥርዓት የተካሄደው የኡጋንዳ ነዳጅ ላይ ትልቅ ድርሻን የያዘው የፈረንሳዩ ሼል ከኡጋንዳ መንግሥት ጋር ታሪካዊ ስምምነት መድረሱን በገለጸበት ማግስት ነው፡፡

የነዳጅ መስመሩ 80 ከመቶ በታንዛኒያ መሬት ላይ ነው የሚያርፈው፡፡ ግንባታው ለ18ሺ ታንዛኒያዊያን የሥራ እድል ይፈጥራል፡፡