ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ እሳት፡ በርካቶች በኦሪጎን ሰደድ እሳት የደረሱበት አልታወቀም
በአሜሪካዋ ኦሪጎን ግዛት በአስርታት የሚቆጠሩ ሰዎች ካጋጠመው የሰደድ እሳት ጋር በተያያዘ የት እንደገቡ ያልታወቀ ሲሆን ከግማሽ ሚሊየን በላይ የሆኑት ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
ይህንን ያሉት አስተዳዳሪዋ ኬት ብራውን ሲሆኑ አክለውም ባዷቸውን የቀሩ ቤቶች እየተዘረፉ መሆኑን አስታውሰው ዜጎች ከአካባቢው ለቅቀው እንዲሄዱ ማሳሰቢያ አስተላልፈዋል።
የኦሪጎን የድንገተኛ አገዳዎች አስተዳደር ዳይሬክተር የሆኑት አንድሪው ፌልፕስ በበኩላቸው ጉዳት ለሚያጋጥማቸው ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የሰደድ እሳቱ እስካሁን ኦሪጎን ውስጥ ብቻ የአራት ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ እስካሁን 11 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። በአሜሪካ በሚገኙ 12 ግዛቶች ውስጥ አንድ መቶ የሰደድ እሳቶች እየተቀጣጠሉ ይገኛሉ።
የኦሪጎን አስተዳዳሪዋ አርብ ዕለት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ '' እስካሁን ባለው መረጃና የግዛቲቱ ፖሊስ ባገኘው መረጃ መሠረት በአስርታት የሚቆጠሩ ሰዎች የት እንደገቡ አልታወቀም፤ በተለይ ደግሞ ጃክሰን፣ ሌን እና ማሪዮን ካውንቲዎች ውስጥ'' ብለዋል።
አክለውም በኦሪጎን ይኖሩ የነበሩ 40ሺ ሰዎችም በአስገዳጅ ሁኔታ ከመኖሪያቸው እንዲለቁ መደረጋቸውን አስታውቀዋል።
''ሰዎች ትተዋቸው የሄዷቸው ቤቶች እየተዘረፉ ስለመሆኑ ጭምጭምታ አለ፤ እናም ይሄ በጣም አሳሳቢና ሰላም የሚነሳ ነገር ነው። ሰዎች መኖሪያ ቤታቸው ይኑር አይኑር ማወቅ አለመቻላቸው ከባድ ነው'' ሲሉም ተደምጠዋል አስተዳዳሪዋ።
በኦሪጎን ግዛት የማሪዮን ካውንቲ ፖሊስ ሰዎች ትተዋቸው የሄዱ ቤቶችን ሰብረው በመግባት ሲዘርፉ የነበሩ ሁለት ግልሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉም ተዘግቧል።
በሰደድ እሳቱ ሕይወታቸው ካለፉት አራት ሰዎች መካከል አንድ ታዳጊና የሴት አያቱ ይገኙበታል። ሰዎቹም የሞቱት በደቡባዊ ፖርትላንድ ሊዮንስ ከሚባለው ስፍራ አቅራቢያ ነው።
በአሜሪካ በሰደድ እሳት ከተጠቁት 12 ግዛቶች መካከል ኦሪጎን፣ ካሊፎርኒያ እና ዋሽንግተን ግዛቶች ክፉኛ እየተሰቃዩ ይገኛሉ።
በዋሽንግተን ባጋጠመው ከፍተኛ የተባለ የሰደድ እሳት ምክንያት አንድ ቤተሰብ ከእሳቱ ለማምለጥ በሚሞክርበት ጊዜ የአንድ ዓመት ሕጻን በመሀል ሕይወቱ ማለፉ ተገልጿል።
ወላጆቹም ቢሆኑ በአሁኑ ሰአት በሆስፒታል ውስጥ በአሳሳቢ የጤና ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።
በካሊፎርኒያ ደግሞ በሰደድ እሳቱ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ ነው። በግዛቲቱ በምትገኘው ቡት ካውንቲ ብቻ ፖሊስ ባለፉት ቀናት የአስር ሰዎችን አስክሬን አግኝቷል።
በተጨማሪ ደግሞ 16 ሰዎች የት እንደገቡ አልታወቀም ተብሏል።