በካሊፎርኒያ ሰደድ እሣት የተከበቡ ሰዎችን ለማዳን ርብርብ ተጀምሯል

በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛት ሰደድ እሳት ተነስቷል።
እሳቱ ሰው ሳይበላ ለመታደግ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ርብርብ ጀምረዋል፥
በአደጋ መከላከል ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች በሄሊኮፕተር በመታገዝ በርካታ ሰዎችን እያስወጡ ነው።
እስካሁን ድረስ ብዙዎችን ከአደጋው ስፍራ ማስወጣት ቢቻልም አሁንም በእሳት ተከበው ያሉ ሰዎች እንዳሉ የግዛቲቱ ባለስልጣናት ይናገራሉ።
በፍጥነት እየተዛመተ ያለው ሰደድ እሳት ባለፈው አርብ ምሽት 12፡45 ግድም ነው የጀመረው።
ፍሬስኖ በተሰኘው ክፍለ ግዛት ውስጥ ካለው ሲዬራ ብሔራዊ ፓርክ የተነሰው እሳት እስካሁን ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት አዳርሷል።
እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት ሁለት ሰዎች ክፉኛ ሲጎዱ ከአስር በላይ ሰዎች መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ፓርኩ ቁልቁለታማ ስለሆነ ሰደድ እሳቱ በፍጥነት እንዲስፋፋ አስተዋፅኦ አድርጓል ይላሉ የአካባቢው አስተዳዳሪዎች።
የፍሬኖስ ክፍለ ግዛት እሳት አደጋ በትዊተር ገፁ በለቀቀው መልዕክት ሄሊኮፕተሮች ወደ ስፍራው በመሄድ በእሳት ተከበው ያሉ ሰዎችን ለማውጣት ጥረት እያደረጉ ነው ብሏል።
ምን ያህል ሰዎች በእሳት ተከበው እንዳሉ ግን እንደማይታወቅ ተነግሯል።
የካሊፎርኒያ ግዛት በታሪኳ አይታው የማታውቀውን ሙቀት እያስተናገደች ነው።
ከሳምንታት በፊት ግዛቲቱ በዓለማችን ከፍተኛ የተባለውን የሙቀት መጠን አስመዝግባ ነበር።
አገረ ገዥ ጋቪን ኒወሶ ባለፈው አርብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግገዋል።
ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ መብራት በፈረቃ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።
ቅዳሜና እሁድ የሙቀት መጠኑ እስከ 49 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
የአሜሪካ ብሔራዊ አየር ትንበያ አገልግሎት በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ጠረፋማ ቦታዎች በጣም አደገኛ የሆነ የሙቀት መጠን ሊያስመዘግቡ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።












