ሰሜን ኮሪያ ለታይፉን አውሎ ንፋስ ዝግጅት አላደረጉም ያለቻቸውን ባለስልጣናት ልትቀጣ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP
በዚህ ሳምንት ረቡዕ የሰሜን ኮሪያ ምስራቃዊ ግዛት በታይፉን አውሎ ንፋስ በከፍተኛ ሁኔታ መመታቷን ተከትሎ የአካባቢው ባለስልጣናት ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተብሏል።
የአገሪቷ ገዢው ሰራተኞች ፓርቲ ልሳን የሆነው ጋዜጣ የባህር ዳርቻዋ ከተማ ወንሳን በታይፉን ማያስክ አውሎ ንፋስ ከመመታቷ ጋር ተያይዞ ባለስልጣናቱ ቅድመ ዝግጅት አላደረጉም በማለት ወንጅሏቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪም "ኃላፊነት የጎደላቸው" በማለትም ጠንከር ባለ ቃል ወቅሷቸዋል።
ጋዜጣው በአውሎ ንፋሱ ምን ያህል ሰዎች እንደጠፉ፣ እንደተጎዱ፣ ወይም እንደሞቱ ዝርዝር መረጃ ባይሰጥም "በርካታዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል" በማለት ጠቅለል ባለ መልኩ አስፍሯል።
የአካባቢው ባለስልጣናት ከገዢው ፓርቲ የተሰጣቸውንም ትዕዛዝ አላከበሩም በማለትም የአውሎ ንፋሱ በሰዎችና በንብረት ላይ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት መከላከል ይቻል እንደነበር ጠቁሟል።
የወንሳን ከተማ ባለስልጣናት በአስቸኳይ በአውሎ ንፋሱ ሊጋለጡ የሚችሉ ቤቶችን እንዲለዩና ነዋሪዎቹን እንዲያስወጡ ትዕዛዝ እንደተላለፈላቸውም ሮዶንግ ሲንመን ጋዜጣ በቅዳሜ እትሙ አስነብቧል።
"ትዕዛዙን ባላከበሩት አመራሮች ላይ ጠበቅ ያለ የፓርቲው፣ አስተዳደራዊና ህጋዊ ቅጣቶች ይጠብቃቸዋል" በሚልም ዘገባው አስነብቧል።
የአካባቢው አመራሮች የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ከማስፈፀም ወደ ኋላ ብለው ነው? ወይስ ህዝቡ ላይ ያስከተለውን ቁጣ ለመቆጣጠር በፓርቲያቸው በኢፍትሃዊ መልኩ ኢላማ ተደርገው ነው የሚለውን ማጣራት እንዳልተቻለ የቢቢሲ እስያና ፓስፊክ አካባቢዎች አዘጋጅ ሲሊያ ሃቶን ተናግረዋል።
የመንግሥት ሚዲያ ኬሲቲቪ በዚህ ሳምነት መጀመሪያ ላይ እንዳሳየው አውሎ ንፋሱና ዶፍ ተቀላቅለው ባስከተለው ጎርፍ ድልድዮችና ህንፃዎች መፈራረሳቸውን ነው።
ከሳምነት በፊት ታይፉን ባቪ በሚባለው የአውሎ ንፋስ ክፉኛ የተመታችው ሰሜን ኮሪያ ይህኛው ደግሞ መደገሙ ከፍተኛ ተፅእኖን ፈጥሯል።
ሰሜን ኮሪያ ተራራማና ከፍተኛ ቦታዎች ባጋጠማቸው የደን መራቆት ለጎርፍ ተጋላጭ አድርጓታል።
ታይፉን ማያስክ በሰሜን ኮሪያ ብቻ ሳይሆን በደቡብ ኮሪያም ቢያንስ ሁለት ሰዎች ገድሏል፤ እንዲሁም ቡሳን ተብላ በምትጠራው ከተማ ውስጥ 2 ሺህ 200 ሰዎችን አፈናቅሏል።












