ሙዚቃ፡ የአር ኤንድ ቢ አቀንቃኙ ኤኮን ሴኔጋል ውስጥ ከተማ ሊገነባ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሴኔጋላዊ- አሜሪካዊው የአር ኤንድ ቢ አቀንቃኝ ኤኮን ሴኔጋል ውስጥ የራሱን ከተማ ሊገነባ መሆኑን ተናገረ።
ድምጻዊው ስለዚህ የከተማ ግንባታ እኤአ ከ2018 ጀምሮ ሲናገር የነበረ ሲሆን፣ ሰኞ እለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የከተማ ግንባታው በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት እንደሚጀመር አስታውቋል።
ኤኮን በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ለከተማ ግንባታው ገንዘባቸውን ያወጡ ባለሃብቶች ማንነትን ይፋ ከማድረግ የተቆጠበ ሲሆን፣ ነገርግን ለግንባታው የሚያስፈልገው አንድ ሶስተኛ ገንዘብ፣ 6 ቢለዮን ዶላር ተገኝቷል ብሏል።
የከተማዋን ሕንጻ ግንባታ ዲዛይን ያደረገውየሰስነ ህንጻ ባለሙያ፣ ሁሴን ባራኪ፣ ከተማዋ 300,000 ነዋሪዎችን መያዝ እንድትችል ተደርጎ እንደምትታነጽ ተናግረዋል።
ኤኮን ከተማዋን ለአፍሪካ አሜሪካውያን እያስተዋወቀው ይገኛል።
እውነተኛ ስሙ አሊኦውኔ ባዳራ ቲያም የሆነው ኤኮን፣ ስለ አፍሪካ አሜሪካውያን ሲናገር " አፍሪካ አሜሪካውያን ባህላቸውን አያውቁም. . .ስለዚህ ከተማውን ለመገንባት የፈለግኩት ከቤታቸው ወደ ቤታቸው እንደመጡ እንዲሰማቸው ለማድረግ ነው" ሲል ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ተናግሯል።
ኤኮን ከሴኔጋላውያን ቤተሰቦች አሜሪካ ውስጥ መወለዱ ይታወሳል።
"ከአሜሪካ ወይንም ከአውሮፓ ወይንም ከሌላ የዓለማችን ክፍል ወደ አፍሪካ ሲመጡ ሴኔጋል የመጀመሪያ መዳረሻቸው እንድትሆን እንፈልጋለን" ማለቱም ተሰምቷል።












