ኢትዮጵያ ፡ ኮቪድ-19 ያሰናከለው ምርጫና ያልተረጋጋው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር

ዓለም አቀፉን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተከትሎ ባይራዘም ኖሮ ባለፈው ቅዳሜ ኢትዮጵያ ውስጥ የምርጫ ቀን ይሆን ነበር።
አንዳንዶች ምርጫው በተራዘመበት ሒደት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ሲሆን፣ ከናካቴው ምርጫው በመራዘሙ ውሳኔ ላይ አልስማማም ያለ የሚመስለው የትግራይ ክልል የራሱን ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ ደፋ ቀና ላይ ነው።
ምርጫው መራዘሙ ይፋ ከሆነበት ከወርሃ መጋቢት አንስቶ ምን ዓይነት የፖለቲካ እና የደኅንነት ለውጦች ተከሰቱ ሲል ቢቢሲ የተለያዩ አካላትን አነጋግሯል።

ሒሩት ክፍሌ ለእስር ባይታወር አይደለችም። የሃምሳ ዓመቷ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሥራ አስፈፃሚ አባል በህይወት ዘመኗ ለአራት ጊዜያት ያህል እስርን ቀምሳለች።
በቅርቡ እንኳ ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ማግስት ከተቀሰቀሰው እና ቢያንስ የ170 ሰዎችን ህይወት ከቀጠፈው ግርግርና ጥቃት ጋር በተያያዘ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በነበረው ሁከት እጇ አለበት ተብላ በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ሃያ አንድ ያህል ቀናትን በእስር ቤት አሳልፋለች።
"ከቀኑ ስድስት ሰዓት ገደማ ይሆናል" ትላለች ሒሩት የተያዘችበትን ሁኔታ ለቢቢሲ ስታስረዳ፤ "አካባቢው ላይ ያልተለመዱ ሰዎች ይተዩ ነበር፤ እና ሰው ተጠራጥሮ ምንድን ናቸው እነዚህ ሰዎች? ሲለኝ ለማየት ነው የወጣሁት። [. . . ] ወደቤቴ ስመለስ ተከታትለውኝ ተመለሱ፤ [. . . ] ፖሊሶች ነን፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ለጥያቄ ይፈልግሻል አሉኝ" ከዚያም ከሦስቱ ፖሊሶች ጋር ጉዞ መጀመሯን ትናገራለች ሒሩት።
እስር ቤት ከገባች በኋላ አንድ ጊዜ ምርመራ እንደተደረገላት፣ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ምግብ ከቤተሰብ ይገባላት እንዳይነበር፣ ጠበቃዋን እንዳላገኘችና የምትቀይረው ልብስ እንዳልነበራት ታስታውሳለች።
ሒሩት የወርሃ ሰኔውን ነውጥ ተከትሎ ከታሰሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች መካከል መፈታት ከቻሉት ጥቂቶች ውስጥ አንዷ ናት።

በብዙዎች በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው አጠቃላይ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መራዘሙን ተከትሎ፤ መዘግየቱ የተሻለ ዝግጅት ለማድረግ ዕድል ሊፈጥር ይችላል ብለው ተስፋ ከሰነቁት መካከል መቀመጫውን ኔዘርላንድስ ያደረገው የፖለቲካ እና የደኅንነት ተንታኙ አደም ካሴ አበበ (ዶ/ር) ይገኝበታል።
ይሁንና በነባራዊነት የታየው ተደጋጋሚ የፖለቲካ እና የደኅንነት ችግሮች ፈጠው መታየታቸው መሆኑ ተንታኙን ቅር አሰኝቷል።
"ቀድሞውኑም ኢትዮጵያ ስሱ የሆነ ሽግግር ላይ ነበረች" የሚለው አደም (ዶ/ር)፤ "የምርጫው መራዘም ለአንዳንድ ተቃዋሚ ቡድኖች አዲስ የሙግት ነጥብ ፈጥሮ ውጥር ብሎ የነበረውን የፖለቲካ እና የደኅንነት ሁኔታ የበለጠ አክርሮታል" ሲል ለቢቢሲ ያስረዳል።
"ውሳኔውን ተከትሎም ምርጫ መቼ ይካሄዳል የሚለውን በመወሰን ረገድ ለፌዴራል መንግሥት ብቸኛ የወሳኝነት ዕድል መስጠቱ እንዲሁም ለተቃዋሚዎች በዚህ ሽግግር ወቅት ምንም ዓይነት ይፋዊ የሆነ ሚናን በመንፈጉ ሙቀቱን የበለጠ ጨምሮታል።"
የአናሳዎች መብት ተቆርቋሪው ማይኖሪቲ ራይትስ እንዳተተው እንዲሁም በሌሎች ዘገባዎች እንደተገለፀው በነውጡ ወቅት በሕዝብ ብዛት በአገሪቱ ቀዳሚ በሆነው የኦሮሚያ ክልል ብሔር እና ሐይማኖትን ያማከለ ጥቃት ደርሷል፣ ሰዎች ተገድለዋል፣ ንብረታቸውም ወድሟል።
ይሄንን ተከትሎም መንግሥት የወሰዳቸው የእስር እርምጃዎች በአንዳንድ በጥቃቶቹ በተደናገጡ ሰዎች ዘንድ ድጋፍን አግኝቶ የነበረ ይመስላል።
ይሁንና እርምጃው የተቃውሞን እንቅስቃሴ ያዳክማል ሲሉ የሚያብጠለጥሉትም አሉ።
ስመ ጥር አባሎቹ የታሰሩበት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀ መንበር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) "ዋናው ነገር መረጋጋትን ወደ አገሪቷ እና ወደ ፖለቲካ ከባቢው መመለስ መሆን አለበት" ይላሉ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ።
"ነገር ግን እየተሄደበት ያለው መንገድ ለማናችንም የሚጠቅም አይደለም። ሰዎቹ የታሰሩበት መንገድ በኦሮሞ ወጣት ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አይመስለኝም። ተቃዋሚን የመጨፍለቅ ሙከራ ተደርጎ የተቆጠረ ነው የሚመስለኝ።"
መረራ (ፕሮፌሰር) ይቀጥሉናም "ችግራችን ፖለቲካዊ ነው፤ መንግሥት እየተከለተለ ያለው መንገድ ግን 'የሕግ የበላይነት' የሚለውን ነው፤ ችግራችን የሕግ የበላይነት አልነበረም፤ ችግራችን የፖለቲካችን ቆሞ ቀር መሆኑ ነው። በተለይ ደግሞ ዲሞክራሲያዊ ሽግግርን ለማሳካት የነበረው ተስፋ መክሸፍ ዋጋ እያስከፈለን ነው።"
የታሰሩ ሰዎች ረዘም ላለ ጊዜ ክስ ሳይመሰረትባቸው መቆየቱ እና ፖሊስ ወይንም ዐቃቤ ሕግ በሚያቀርቧቸው ተደጋጋሚ የተጨማሪ ቀን ይሰጠን ጥያቄዎች የፍርድ ሒደቱ መጓተቱ ሌላኛው መንግሥት ላይ የሚቀርብበት ትችት ነው።
ይህንን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሰክሬታሪ ቢሮ ለቢቢሲ በላከው የጽሁፍ ምላሽ የደረሰው ውደምት ስፋት እና ጥልቀት ጊዜን የሚወስድ እና አንጡራ ሀብትን የሚጠይቅ ምርመራ መጠየቁን ገልጿል። ይህ የሚከናወነውም አገሪቷ ከዓለም አቀፉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ግብግብ በተያያዘችበት ወቅት መሆኑን ጨምሮ አስረድቷል።
"በታላቅ ጥረት እና ትጋት ሕግ አስከባሪ ተቋማታችን የምርመራ ሒደቱን በመቋጨት ላይ ይገኛሉ" የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት እንደ አብነትም በታዋቂ የፖለቲካ ሰዎች ላይ የምርመራ ሥራ ተጠናቅቆ የቅድመ-ክስ የችሎት ሒደት መጀመሩንም ያነሳል።
ይህ የሆነበት ምክንያትም ፖለቲከኞቹ ያላቸውን ገዘፍ ያለ ተፅዕኖ በመጠቀም ምስክሮች ላይ ጫና ሊያሳድሩ ይችላሉ የሚል ስጋት በመፈጠሩ መሆንን ይናገራል።
"መንግሥት በቅርቡ በአንዳንድ የፖለቲካ ሰዎች የተለኮሱ የነውጥ ክስተቶች በእርግጥም በዲሞክራሲያዊ ሽግግራችን ላይ አደጋን የደቀኑ ናቸው ብሎ ያመናል" የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ "ኃላፊነት በጎደለው አኳኋን ለሚንቀሳቀሱ፤ አገሪቱን የሚያስተዳድረውን ሕግ ከቁብም ለማይቆጥሩ የተቃውሞ ፖለቲከኞች መንግሥት ምላሽ ሲሰጥ ከፍ ያለ ቁጥብነትን ቢያሳይም፤ እንዲህ ያለው ቁጥበነት ግን ከዚህ ወዲያ የሚኖር አይሆንም" ብሏል።

ኢትዮጵያ አሁንም ከፖለቲካዊ ውጥረት የተገላገለች አትመስልም። ከሁለት ሳምንታት በፊት እንኳ በኦሮሚያ ክልል የተቃውሞ ሰልፎች ተስተውለዋል፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ ሰዎች ተገድለዋል፤ ሌሎችም ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የተጠረጠርችበትን ወንጀል የምታስተባብለውና የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ሒሩት ክፍሌ ተደጋጋሚ እስርን የምትቀምሰው ከፖለቲካ ተሳትፎዋ ጋር በተያያዘ መሆኑን ታምናለች። ረጅሙ በእስር ቤት ያሳለፈችው ጊዜ ሰባት ዓመታትን ያህል ነው።
በወቅቱ የአስራ ዘጠኝ ዓመት እስር ተፈርዶባት የነበረ ቢሆንም ለበርካታ ወራት የዘለቀ ሕዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ በ2010 ዓ.ም የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ከመወሰናቸውም በተጨማሪ በርካታ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና የሐይማኖት መሪዎች ከእስር እንዲፈቱ ሲወሰን እርሷም ለቤቷ በቃች።
ወዲያውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ይፋ የተደረጉ የማሻሻያ እርምጃዎችን ስታይ የእስር ዘመን አበቃ ብላ አስባ እንደነበር ትናገራለች፤ አሁን ግን "ብዙም እርግጠኛ አይደለሁም" ትላለች።


















