ህንድ ፡ በተቀደሰው ድልድይ ላይ እርቃኗን ቪዲዮ የተቀረፀችው ፈረንሳያዊት ሴት በቁጥጥር ስር ዋለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንዲት የፈረንሳይ ዜጋ ህንድ ውስጥ በሚገኝ ድልድይ ላይ እራሷን በቪዲዮ ስትቀርጽ በቁጥጥር ስር ዋለች።
ፈረንሳያዊቷ በቁጥጥር ስር የዋለችው በሰሜናዊቷ ሪሺኬሽ ከተማ በሚገኘው የተቀደሰ ድልድይ ላይ እርቃኗን በመሆን ራሷን ቪዲዮ ቀርጻለች በሚል ነው።
ይህ በላክሽማን ጅሁላ ድልድይ ላይ የተቀረፀ ተንቀሳቃሽ ምስል ደግሞ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ ተለጥፏል።
ግለሰቧ የህንድ የበይነ መረብ ሕግ ተገላብጦ፣ አንቀጽ ተጠቅሶባት የምትከሰስ ሲሆን፤ ጥፋተኛ ሆና ከተገኘች እስከ ሦስት ዓመት ድረስ ወህኒ ልትሰነብት እንደምትችል የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ዘገባ ያስረዳል።
ድልድዩ በጋንጀስ ወንዝ ላይ የተዘረጋ ሲሆን ቅዱስ ስፍራ ከመሆኑ በተጨማሪም የአገር ጎብኚዎች የሚያዘወትሩት ስፍራ ነው።
ግለሰቧ በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ የዋስትና መብቷ ተጠብቆላት ከወህኒ የወጣች ሲሆን ቪዲዮውን የተቀረፀችው የጌጣ ጌጥ ንግዷን ለማስተዋወቅ ነው ተብሏል።
ፈረንሳያዊቷ በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ የተወሰደችበት ፖሊስ ጣብያ አዛዥ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ሲናገሩ "ምናባት በፈረንሳይ እንዲህ ዓይነት ነገር ተቃውሞ አያስነሳ ይሆናል። ግን ሪሺኬሽ ቅዱስ ስፍራ ነው እናም ላክስማን ጅሁላ ራም (የህንዱ አማልክት)፣ እና ወንድሙ ላክሽማን እንዲሁም ባለቤቱ ሲታ ጋንጀስን ያቋረጡበት ነው" ብለዋል።
የግለሰቧ ማንነቷ ያልተገለፀ ሲሆን፣ ፖሊስ መረጃው ከደረሰው በኋላ ሐሙስ እለት በቁጥጥር ስር መዋሏ ታውቋል።
ሌላ ፖሊስ ደግሞ "የእምነት ክህደት ቃሏን ስንቀበላት እርቃኗን የምትታይበትን ተንቀሳቃሽ ምስሉን ራሷ መቅረጿን አምናለች፤ ነገር ግን በህንድ ሕገ ወጥ መሆኑን እንደማታውቅ ነው የተናገረችው። ተንቀሳቃሽ ምስሉም ሆነ ፎቶዎቹ የአንገት ጌጥ ንግዷን ለማስተዋወቅ ብላ የተነሳችው መሆኑንም ጨምራ ተናግራለች" ሲል ለሂንዱስታን ታይምስ ጋዜጣ ተናግሯል።
የይህ ጉዳይ ፍርድ ቤት ቀርቦ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ወራት ሊወስድ ይችላል ተብሏል።














