ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ግብጽ አንዲት ሴትን ደፍረው ከአገር የወጡ ተጠርጣሪዎችን ለማስመለስ እየጣረች ነው
በግብጽ ዋና ከተማ ካይሮ በሚገኝ አንድ ቅንጡ ሆቴል አንዲት ወጣት ሴትን በቡድን በመድፈር የተጠረጠሩ ግለሰቦች አገር ለቀው መውጣታቸውን የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።
ዐቃቤ ሕግ እንዳለው ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ሰባቱ ግለሰቦች ስለተፈፀመው ወንጀል በኢንተርኔት ላይ ዘገባዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ሐምሌ ወር ላይ አገር ጥለው ሸሽተዋል።
ይህ የሆነው ጥቃቱ የተፈጸመባት ግለሰብ ክስ ከማቅረቧ ከአንድ ወር በፊት መሆኑን የጠቀሰው ዐቃቤ ሕግ፤ ሰባቱን ተጠርጣሪዎች ተከታትሎ በቁጥጥር ሥር ለማዋል አገሪቷ ዓለም አቀፋዊ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው ብሏል።
ቀሪዎቹ ሁለት ተጠርጣሪዎችም እየተፈለጉ መሆኑንም ገልጿል።
የመድፈር ወንጀሉ የተፈፀመው ከ6 ዓመታት በፊት ካይሮ በሚገኘው ፌርሞንት ናይል ሲቲ ሆቴል ነበር። ዘጠኙ ግለሰቦችም የተጠረጠሩት አንዲት ወጣት ሴትን በእፅ በማደንዘዝና በቡድን በመድፈር ወንጀል ነው።
ስለጥቃቱ መፈጸም የተሰማው ለተደፈረችው ሴት ፍትሕን በሚጠይቀው 'አሳልት ፖሊስ' በተባለው የኢንስታግራም ገጽ ነበር።
በዚህ ገጽ ላይ የሰፈረው ፅሁፍም በሆቴሉ ከተካሄደ የመዝናኛ ድግስ [ፓርቲ] በኋላ የቱጃር ቤተሰብ አባላት የሆኑ ስድስት ግለሰቦች አንዲትን ሴት በእፅ አደንዝዘው እንደደፈሯት ያስረዳል።
ድርጊቱን በማውገዝ ከተካሄደው 'ሚ ቱ' የተሰኘ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻን ተከትሎ የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ ወንጀሉን በመፈፀም የተጠረጠሩት ግለሰቦች እንዲታሰሩ ትዕዛዝ አውጥተው ነበር።
ዐቃቤ ሕግ ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫውም በግለሰቦቹ ላይ የእስር ትዕዛዝና የጉዞ እገዳ አውጥቶ እንደነበር የገለፀ ሲሆን ግለሰቦቹ በቁጥር ስንት እንደሆኑና ማንነታቸው ግን አልጠቀሰም ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ተጠቂዎች ጉዳዩን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከመልቀቃቸው በፊት አቤቱታቸውን ለሚመለከተው አካል እንዲያቀርቡ አሳስቧል።