ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትግራይ ምርጫ፡ '2.6 ሚሊዮን መራጭ ተመዝግቧል'
የትግራይ ክልል ምርጫ በመጪው ጳጉሜ አራት በሚካሄደው ምርጫ ላይ ለመሳተፍ እተደረገ ባለው የመራጮች ምዝገባ 2̂ ሚሊዮን ሕዝብ እንደተመዘገበ የምርጫው አስተባባሪ አካል አስታወቀ።
ከክልሉ ምክር ቤት ይሁንታ አግኝቶ በቅርቡ የተቋቋመው የምርጫ ኮሚሽን የመራጮች ምዝገባ ማከናወን የጀመረው ባለፈው ሳምንት ነበር።
መደበኛው የመራጮች ምዝገባ ዛሬ የሚጠናቀቅ ቢሆንም በተለያየ ምክንያት መመዝገብ ያልቻሉ ሰዎች ቅዳሜና እሁድ መመዝገብ እንዲችሉ ዕድል መመቻቹትን ኮሚሽነር ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እስከዛሬ [ነሃሴ 21/2012] ባለው ጊዜ 2.6 ሚሊዮን መራጮች መመዝግባቸውን ኮሚሽነሩ ይናገራሉ። ይህም በትግራይ ክልል ታሪክ ትልቁ የመራጮች ቁጥር ነው ይላሉ።
በአዲሱ ዓመት ዋዜማ የሚከናወን የትግራይ ክልል ምርጫን እንዲታዘቡ በሚል ኮሚሽኑ ለሃገር ውስጥና ለሃገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
መቀሌ የሚገኘው የቢቢሲ ባልደረባ የምርጫ ምዝገባው ባለፈው አርብ ሲጀመር በአሸንዳ በዓል ምክንያት ብዙም ሰው ሲመዘገብ ባይስተዋልም በዚህ ሳምንት ግን በርካቶች ወደ መምዘገቢያ ጣቢያዎች ሲተሙ ተመልክቷል።
የምርጫ መመዝገቢያ ጣብያዎች ድምፅ ሰጪዎች ለመመዝገብ ሲመጡ የአፍና አፍንጫ ጭምብል እንዲያጠልቁና ወደ ውስጥ ሲዘልቁ እጃቸውን በሳኒታይዘር እንዲያፀዱ እንደሚመክሩ ባልደረባችን ታዝቧል።
ባለፈው ሳምንት መግለጫ የሰጡት የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መረሳ ፀሐዬ 3 ሚሊዮን መራጭ ሊመዘገብ ይችላል ብለው እንደሚገምቱ ተናግረው ነበር።
በክልሉ ለድምፅ መስጫ የሚሆኑ 2 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች ተሰናድተዋል።
ምርጫውን ለመታዘብ ከ60 በላይ የተለያዩ አካላት መመዝገባቸው የትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽን ሕዝብ ግነኙነት ኃላፊ አቶ አቤል ግኡሽ ለቢቢሲ ገለጸው፤ በርካታ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ምርጫውን እንዲታዘቡ ጥሪ ማድረጋቸው አመልክተዋል።
በክልሉ ውስጥ ያሉ ሲቪክ ማኅበራትም ምርጫውን ለመታዘብ እየተመዘገቡ ሲሆን እስካሁን ከ60 በላይ ታዛቢዎችን ማመልከቻ መቀበላቸውን ገልፀዋል።
እነዚህ መካከል ሲቪክ ማኅበራት፣ በሰሜን አሜሪካ የትግራይ ተወላጆች ማኅበር፣ ሌሎች የማኅበረሰብ ድርጅቶችና በትግራይ ያሉ የሐይማኖት ተቋማት ጥምረት እንደሚገኙበትና ቁጥራቸው ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል አቶ አቤል ገልጸዋል።
ገዥው ፓርቲ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይን ጨምሮ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከቀናት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ፓርቲዎቹ የመጀመሪያውን የምርጫ ክርክር በመገናኛ ብዙሃን በተላለፈ የቀጥታ ሥርጭት አከናውነዋል።
ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ገዥው ፓርቲ ሕወሓት ላለፉት 27 ዓመታት መሰዋዕትነት የተከፈለበትን የትግራይ ጥቅም አላስጠበቀም፤ እንዲሁም የክልሉን ሕዝብ ረስቶት ነበር ሲሉ ወቅሰዋል።
በክርክሩ ላይ የተሳተፉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለትግራይ ነፃነት አሊያም በኮንፌዴሬሽን ከሌሎች ክልሎች ጋር አብሮ ለመኖር እንደሚታገሉ ይፋ አድርገዋል።
ነገር ግን አሲምባ የተሰኘው ፓርቲና ገዥው ሕወሓት ከሦስቱ ፓርቲዎች [ባይቶና፣ ሳልሳይ ወያነ፣ ውናት] በተፃራሪ እንደ ሃገር አብሮ መቀጠል የሚለውን ሐሳብ ሲያንፀባርቁ ተስተውለዋል።
በምርጫው ለመወዳደር ከተመዘገቡ 11 የግል ተወዳዳሪዎች መካከል ስድስት ግለሰቦች በተለያዩ ምክንያቶች ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸው ከቀናት በፊት ተዘግቧል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ቢራዘም ምርጫውን ለማካሄደው የወሰነው የትግራይ ክልል ጳጉሜ 4/2012 ምርጫውን ያከናውናል።