ፌስቡክ ፡ ነብዩ መሐመድን በሚያንቋሽሽ የፌስቡክ ጽሁፍ ሰበብ በተነሳ ረብሻ በሕንድ 3 ሰዎች ሞቱ

አንድ ግለሰብ ፌስቡክ ላይ ያሰፈረውን መልዕክት ተከትሎ በሕንድ ሦስተኛ ከተማ ባንግሎር ውስጥ በተቀሰቀሰ ሦስት ሰዎች ተገድለዋል።
ግጭቱ የተነሳው አንድ የአካባቢው ፖለቲከኛ ዘመድ በፌስቡክ ገጹ ላይ ነብዩ መሐመድን የሚያንቋሽሽ ያልተገባ መልዕክት ጽፏል በሚል ነው።
ተቃዋሚዎች በዚህ ፖለቲከኛ ቤት ተሰብስበው ፍትህ ይሰጠን ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
ሌሎች የተቆጡ ሰልፈኞች በበኩላቸው ተሸከርካሪዎችን አቃጥለዋል። በአካባቢው ነገር ለማብረድ የመጡ ፖሊሶችም ላይ ከፍ ያለ ጥቃት ሰንዝረዋል።
ቢቢሲ ሂንዲ ከስፍራው እንደዘገበው ፖሊስ ነብዩ መሐመድን በፌስቡክ ሰሌዳው ላይ አንቋሿል ያለውን ግለሰብና ሌሎች 110 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል።
የባንግሎር ከተማ ፖሊስ ኮሚሽነር ከማል ፓንት ለቢቢሲ ሂንዲ እንደተናገሩት ተቃዋሚዎች በትናንትና ነውጥ በትንሹ 60 ፖሊሶች ላይ ጉዳት አድርሰዋል።
ይህን ተከትሎ በሁለት ወረዳዎች ላይ ሰዓት እላፊ ታውጇል።
ፖሊስ በተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስና የፕላስቲክ ጥይቶችን ተኩሷል። ተቃውሞው በዚህ ሊበተን ስላልቻለ ግን ገዳይ ጥይቶችን ለመተኮስ ተገዷል።
ሦስት ሰዎች ስለመሞታቸው የካርናታካ የአገር ውስጥ ገዥ አረጋግጠዋል። ባንግሎር የካርናታካ ክፍለ ግዛት ዋና ከተማ ናት።
ግለሰቡ በፌስቡክ ሰሌዳው ላይ ነብዩ መሐመድን አስመልክቶ የጻፈው ጽሑፍ ወዲያውኑ መነሳቱን ፖሊስ አስታውቋል።
ሚኒስትር አካንዳ ሙርቲ በቪዲዮ ባቀረቡት ተማጽኖ ለተቃዋሚዎቹ ፍትህ እንደሚያገኙ ቃል ገብተዋል።
"ለሙስሊም ወንድሞቼ የምማጸነው ሕግ በተላለፈ ሰው ምክንያት ሕግ እንዳትተላለፉ ነው። ምንም ይሁን ምን ወንድማማቾች ነን። እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ አጥፊው ፍርድ ቤት ቀርቦ ይቀጣል፤ ይህን አረጋግጥላችኋለው" ብለዋል ሚኒስትሩ።














