አውስትራሊያ ፡ የሒትለርን ቪዲዮ በመጠቀም ፌስቡክ ላይ በአለቆቹ የተሳለቀው ሠራተኛ 200 ሺህ ዶላር ተሰጠው

የፎቶው ባለመብት, Downfall
ስኮት ትሬሲ ይባላል፡፡ የግዙፉ የብሪቲሽ ፔትሮሊየም ኩባንያ (ቢፒ) ሠራተኛው ነበር፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ከዕለታት በአንዱ ከሥራ ይባረራል፡፡
የተባረረው አርፍዶ ሥራ በመግባቱ ወይም እንዝህላል ሆኖ አይደለም፡፡ የገዛ መሥሪያ ቤቱ ላይ በመሳለቁ እንጂ፡፡
የተሳለቀበት መንገድ ግን ሳያስበው ዝነኛ አድርጎታል፡፡
ሰውየው በፌስቡክ ለቅርብ ጓደኞቹ አንድ ቪዲዮ ያጋራል፡፡ ቪዲዮው የተወሰደው 2004 ዓ.ም ላይ ዝነኛ ከነበረው ዳውንፎል (Downfall) የሆሊውድ ፊልም ላይ የተቀናበረ ነው፡፡
በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ በሰራተኛውና በአለቆች መካከል የነበረውን የደመወዝ ይጨመርልን ጥያቄና አታካራ ተመርኩዞ አለቆቹ ልክ እንደ ሂትለር ሆነው ሲቆጡ የሚያሳይ ቅንብር ነበር የሰራው፡፡
ይህንን ስላቀ-ምሥል (meme) ለቅርብ የፌስቡክ ጓደኞቹ ብቻ በማጋራቱ አለቆቹ ሰምተው በመቆጣታቸው መሥሪያ ቤቱ ሰውየውን ከሥራ ያባርረዋል፡፡
ሰውየው በዚህ ይናደድና ኩባንያውን ፍርድ ቤት ይገትረዋል፡፡
እንዴት በፌስቡክ ላይ ለጓደኞቼ በቀለድኩት ጥሩ ቀልድ ከሥራ እባረራለሁ ሲል ይከሳል፡፡
በቅድሚያ የመሥሪያ ቤቱ የሰራተኛ ማኅበር ጉዳዩ በሽምግልናና ግልግል ዳኝነት ይታይ ይልና ይኸው ይደረጋል፡፡
የግልግል ዳኝነቱ የሰውየው መባረር ትክክል ነው ብሎ ይፈርዳል፡፡
ሚስተር ትሬሲ ድሮም እናንተን ማመን ይልና ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይዞት ይሄዳል፡፡
ለሁለት ዓመት ያህል ጠበቃ አቁሞ ሽንጡን ገትሮ ከተከራከረ በኋላ ፍርድ ቤት ሰውየው ያለ አግባብ ነው የተባረረው ሲል ይበይንለታል፡፡
በዚህም የተነሳ የብሪታኒያ ፔትሮል ኩባንያ (ቢፒ) ለሰራተኛው 200ሺህ ዶላር እንዲከፍለው ይወስንለታል፡፡
ይህም ላለፉት ሁለት ዓመታት ያጣውን ደመወዙንና ጥቅማጥቅሙን ጨምሮ የጡረታ አበሉንና የሞራል ጉዳት ካሳን ያካተተ ነው፡፡
ቢፒ የሚለው ሰውየው የሂትለርን ቪዲዮ (ምንም እንኳ ከፊልም የተወሰደ ቢሆንም) ተጠቅሞ በመሥሪያ ቤቱ ላይ ምሥለ-ስላቅ ሰርቶ በፌስቡክ ገጽ መለጠፉ ‹አሳፋሪም ነውርም› ነው፡፡
ከአንድ ትጉህ፣ ጨዋ ሠራተኛም የሚጠበቅ አይደለም፡፡
ሚስተር ትሬሲ በበኩሉ እኔ ይህን ያደረኩት መጥፎ ልቦና ይዤ ሳይሆን ለቀልድ ነው፤ ቀልድ ደግሞ ለጤና ጥሩ ነው ብሏል፡፡
ፌዴራል ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን ምሥለ-ስላቁ ላይ ያለው ሂትለር የቢፒ መሥሪያ ቤት አለቆችን አይወክልም፡፡ ስለዚህ ሚስተር ትሬሲ ነውረኛ ሊባል አይችልም ብሏል፡፡
ሰኞ ወደ ሥራ የተመለሰው የነዳጅ አውጪ ሰራተኛው ሚስተር ትሬሲ አካውንቱ ውስጥ 200ሺህ ዶላሩ ከገባለት በኋላ ዘንጦ ነው፡፡
ቢፒ ለሚስተር ትሬሲ 150 ሺህ ዶላር ብቻ ይበቃዋል፣ ምክንያቱም ሰራተኛው ባሰራጨው ቪዲዮ ስማችን ጎድፏል፣ በዚያ ላይ በፍርድ ቤት ክርክር ላይ ሳለ ሥራ ፈልጎ ማግኘት ይችል ነበር።
በዚያን ጊዜ ለቦዘነው እኛ የመክፈል እዳ የለብንም ቢልም የሰራተኛው ጠበቃ በበኩሉ በዚያን ጊዜ ሥራ እንዳልፈለገ በምን አወቃችሁ ሲል ተከራክሯል፡፡
የግራ ቀኙን የሰማው ፍርድ ቤት ‹በቃ 200 ሺህ ዶላር› ለሰውየው ክፈሉት ብሏል፡፡ ገንዘቡ ሲሰላ ወደ ሳባት ሚሊዮን ብር ይጠጋል፡፡















