ስፔን፡ በሙስና እየተወነጀሉ ያሉት ንጉስ ጁዋን ካርሎስ አገር ጥለው አቡዳቢ ገቡ ተባለ

ንጉስ ጁዋን ካርሎስ በአቡዳቢ

የፎቶው ባለመብት, NIUS

ታትሟል

የቀድሞው የስፔን ንጉስ ጁዋን ካርሎስ ከተከፈተባቸው የሙስና ምርመራ ጋር ተያይዞ አገራቸውን ለቀው ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አቅንተዋል ተብሏል።

ኤንአይዩኤስ የተባለው የስፔን ሚዲያ ቡድን የቀድሞው ንጉስ አቡዳቢ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የሚያሳይ ፎቶም ይዞ ወጥቷል።

ንጉስ ጁዋን ካርሎስ አገራቸው ስፔንን ለቅቄ እሄዳለሁ የማለታቸው ዜና በርካቶችን ከሰሞኑ አስደንግጧል።

ንጉሱ ምንም ስህተት እንዳልፈፀሙና አቃቤ ህግም ለጥያቄ ከፈለጋቸው ለመተባበርም ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀው ነበር።

ስፔንን ለቀው መሄዳቸው በዘውዳዊው ስርአት ላይ ከፍተኛ ክርክርና ውዝግብም አስከትሏል፤ ንጉስ ካርሎስም የት ናቸው የሚለው ላይም በርካቶች የተለያየ አስተያየት እየሰጡ ነው።

የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ወደ ዶሚኒካን ሪፐብሊክ፣ ካሪቢያን ደሴቶችና የስፔን ጎረቤት ወደሆነችው ፖርቹጋል ሄደዋል የሚሉ ዘገባዎችንም አስነብበዋል።

ነገር ግን አዲስ የወጡት መረጃዎች እንደሚያሳዩት ንጉስ ጁዋን ካርሎስ በአቡዳቢ ባለ አምስት ኮከቡ ኤምሬትስ ፓላስ ሆቴል ውስጥ እንዳሉ ነው።

አንድ ሙሉውን ፎቅ ተቆጣጥረዋልም ተብሏል።

ንጉስ ካርሎስ ከአቡዳቢው አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው።

ነገር ግን አሁንም ቢሆን በርግጠኝነት ያሉበት ቦታ አልታወቀም። የስፔን የልዑላውያን ቤተሰብም ሆነ መንግሥት ንጉስ ካርሎስ ያሉበትን ቦታ አስመልክቶ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ንጉሥ ካርሎስ ከጎርጎሳውያኑ 1975 ጀምሮ ለአርባ ዓመታት ስፔንን በንግሥና ከመሩ በኋላ በ2014 ነበር ስልጣነ መንበሩን ለልጃቸው ያስተላለፉት፡፡

ስልጣኑን ለልጃቸው የሰጡት የሴት ልጃቸው ባለቤት ጋር ተያይዞ በተነሳ የሙስና ውንጀላ ነው። ስፔን የምጣኔ ኃብት ቀውስ በነበረችበት ወቅት የዝሆን አደን በማካሄድ ቅንጦታዊ ድርጊት ፈፅመዋል የሚል ውዝግብም ተከትሎ ነው።

እነዚህ ውዝግቦች በዚሁ አላቆሙም። ከወራት በፊትም የስፔን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ንጉሱ ከሳዑዲ አረቢያ የፈጣን ባቡር ግንባታ ጋርም ተያይዞ በሙስና ምርመራ ከፍቶባቸዋል።

ይህንንም ተከትሎ የቀድሞው ንጉስ ያለመከሰስ መብታቸውን አጥተዋል።

ከቀናት በፊትም የ82 አመቱ ንጉስ ካርሎስ ለልጃቸው ፍሊፕ ካርሎስ ስድስተኛ በፃፉትም ደብዳቤ ነው አገር ጥለው እንደሚሄዱ ውሳኔያቸውን ያሳወቁት።

የስፔንን ህዝብንም ሆነ ተቋማቱን በበለጠ ለማገልገል አገር ጥለው እንደሄዱ የጠቆመው ደብዳቤው እሳቸው በሌሉበትም መንገድ ልጃቸው በተረጋጋ መንገድ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበውታል።