ደቡብ ኮሪያ ወደ ሰሜን ኮሪያ ሸሽቶ የሄደው ግለሰብ ኮቪድ-19 አልተያዘም አለች

ታትሟል

በኮሮናቫይረስ መያዙ የተጠረጠረው የመጀመሪያው ሰሜን ኮሪያዊ ነጻ መሆንኑን በምርመራ ማረጋገጧን ደቡብ ኮሪያ ገለፀች።

ግለሰቡ ከሰሜን ኮሪያ ወደ ደቡብ ኮሪያ ከሦስት ዓመታት በፊት መምጣቱ የተገለፀ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ግን ወደ ትውልድ አገሩ ተመልሶ ነበር።

ግለሰቡ ከደቡብ ኮሪያ ወደ ሰሜን ኮሪያ የተሻገረው በደቡባዊ ደሴቲ አካባቢ በሚገኝ የቱቦ ማስተላለፊያ ውስጥ በመሹለከለክና በመዋኘት ነበር።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ሰሜን ኮሪያ በኮቪድ-19 የተጠረጠረ ሰው ማግኘቷን አሳውቃ ነበር።

የአገሪቱ መንግሥት የዜና አገልግሎት እንደዘገበው በሽታው እንዳለበት የተጠረጠረው ግለሰብ ከሦስት ዓመት በፊት ወደ ደቡብ ኮሪያ ከድቶ ሄዶ የነበረ ሲሆን በቅርቡ በድንበር በኩል ወደ ሰሜን ኮሪያ ከተመለሰ በኋላ የወረርሽኙ ምልክቶች ታይተውበታል።

ይህንንም ተከትሎ የአገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ-ኡን ከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸውን ሰብስበው ከደቡብ ኮሪያ ጋር በምትዋሰነው የድንብር ከተማዋ ኬሶንግ ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲጣል ተደርጓል።

ሰኞ ዕለት የደቡብ ኮሪያ ጦር የ24 ዓመቱ ወጣት ከሰሜን ኮሪያ ወደ ጋንጋህዋ ደሴት የደረሰው በድንበር አቅራቢያ መሆኑን ገልጿል።

ግለሰቡ ወደ ሰሜን ኮሪያ በዋና ከማቋረጡ በፊት ወደ ቢጫ ባህር በሚወስደው የውሃ መውረጃ ቱቦ ውስጥ እየዳሃ መሄዱን አክለው አብራርተዋል።

"በኬሶንግ ከተማ ድንገተኛ ነገር ተከስቷል፤ ከሦስት ዓመት በፊት ወደ ደቡብ ኮሪያ ኮብልሎ የነበረ ግለሰብ በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ተሻግሮ ወደ አገሪቱ ከገባ በኋላ ቫይረሱ እንዳለበት ተጠርጥሯል" ሲል የየአገሪቱ ዜና ወኪል ኬሲኤንኤ ዘግቧል።

ቅዳሜ ዕለት በተካሄደው የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት አስቸኳይ ስብሰባ መሪው ኪም ጆንግ-ኡን የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር "ከፍተኛ የአስቸኳይ ጊዜ ሥርዓት" እንዲዘረጋ አዝዘዋል።

በተጨማሪም ዜና ወኪሉ እንደዘገበው መሪው ኪም ጆንግ-ኡን በበሽታው የተጠረጠረው ግለሰብ በከፍተኛ ጥበቃ ስር ባለው የድንበር አካባቢ ከደቡብ ወደ ሰሜን ኮሪያ እንዴት አልፎ ሊገባ እንደቻለ እንዲመረመር ያዘዙ ሲሆን፤ ተጠያቂ የሚሆኑ ሰዎች ላይ "ከባድ የቅጣት እርምጃ" እንዲወሰድባቸው አዘዋል።

የደቡብ ኮርያ ከፍተኛ የጤና ባለስልጣን የግለሰቡን ጤንነት በተመለከተ ሲናገሩ "ግለሰቡ በኮቪድ-19 መያዙ፣ አልያም ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት እንዳለው አልተመዘገበም" ብለዋል ለዩንሃፕ ዜና ወኪል።

ከእርሱ ጋር ቅርበት ያላቸው ሁለት ሰዎች ተመርምረው ነጻ መሆናቸው ተረጋግጧል ብለዋል።

ደቡብ ኮሪያ ከቻይና ቀጥሎ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተከሰተባት ብትሆንም በፍጥነት በቁጥጥር ስር አውላዋለች።

ከ50 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ደቡብ ኮርያ በአማካኝ በቀን 50 አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን እያገኘች ሲሆን፤ ከእነርሱም መካከል አብዛኛዎቹ ከሌላ አገር የመጡ ግለሰቦች ናቸው ተብሏል።

ሰሜን ኮርያ ግን እስካሁን ድረስ አንድም ሰው በኮቪድ-19 መያዙን አላሳወቀችም።

ከደቡብ ኮሪያ ወደ ሰሜን ኮሪያ ሸሽተው የሚሄዱ ሰዎች በብዛት ባይኖሩም ከ2015 ወዲህ 11 ሰዎች መሄዳቸው ተመዝግቧል። አሁን ከደቡብ ኮርያ ወደ ሰሜን ኮሪያ የተሻገረው ግለሰብ ማንነት በሚገባ ከተጣራ በኋላ እውነት መሆኑ ከተረጋገጠ 12ኛ ይሆናል ማለት ነው።

ከስድስት ወራት በፊት ቫይረሱ በዓለም ዙሪያ መስፋፋት በጀመረበት ጊዜ ሰሜን ኮሪያ ድንበሮቿን ዘግታ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ለይቶ ማቆያ ውስጥ አስገብታለች።

በዚህ ወር መጀመሪያ ገደማ ላይ መሪው ኪም ጆንግ-ኡን አገራቸው በኮሮናቫይረስ ላይ "አንጸባራቂ ስኬት" እንደተቀዳጀች አሳውቀው ነበር።