ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በትግራይ ምርጫ ለመሳተፍ የሚፈልጉ በሦስት ቀናት ውስጥ እንዲመዘገቡ ጥሪ ቀረበ
ከቀሪው የአገሪቱ ክፍል በተለየ ስድስተኛውን ዙር ምርጫ ለማካሄድ በተወሰነበት በትግራይ ክልል ውስጥ በሚካሄደው ምርጫ ለመወዳደር የሚፈልጉ የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዲመዘገቡ ጥሪ እንደቀረበ ተገለጸ።
በቅርቡ በክልሉ ምክር ቤት የተቋቋመው የትግራይ ምርጫ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት በመጪው ነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ሊካሄድ በታቀደው ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ለሚፈልጉ ፓርቲዎች ጥሪ አቅርቧል።
በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ ነሐሴ መጨረሻ ላይ በሚካሄደው ምርጫ ላይ ለመወዳደር የሚፈልጉ በሙሉ ቀርበው እንዲመዘገቡ ይፋዊ ጥሪ አቅርቧል።
በጥሪው መሰረት በምርጫው ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ የፖለቲካ ድርጅቶችና የግል ተወዳዳሪዎች ከማክሰኞ (ሐምሌ 21/2012) እስከ ሐሙስ (ሐምሌ 23/2012) ባሉት ሦስት ቀናት ውስጥ ሊመዘገቡ እንደሚችሉ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መምህር ሙሉወርቅ ኪዳነ ማርያም ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በምርጫው መሳተፍ ለሚፈልጉ ወገኖች ቀርበው እንዲመዘገቡ ጥሪ ከማቅረብ ውጪ ለምርጫው አፈጻጸም ስለሚያስፈልጉ የጊዜ ሰሌዳና ሌሎች ወሳኝ ነገሮች እስካሁን ያለው ነገር የለም።
ምርጫው ሊካሄድበት ይችላል ስለተባለው ትክክለኛ ቀንም እስካሁን የተገለጸ ነገር ባይኖርም ቢቢሲ ኮሚሽነሩን ስለዚሁ ጉዳይ ጠይቆ፤ ምርጫው የሚካሄድበት ቀንን ከሚመዘገቡ ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር በመወያየት እንደሚወሰን መምህር ሙሉወርቅ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ በክልላዊ ምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎችን ለምዝገባ ከመጥራት ውጪ፣ ለምዝገባ የሚያስፈልጉ ዝርዝር ነገሮች ምን ምን እንደሆነ አልገለፀም።
የትግራይ ክልል ሊያካሂድ ያሰበው ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ሁሉ ላለመሳተፍ የወሰኑ ድርጅቶችም አቋማቸውን አሳውቀዋል።
በተናጠል ይካሄዳል እየተባለ ባለው ክልላዊ ምርጫ ላይ እንደሚሳተፉ ካሳወቁት የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የክልሉ ገዢ ፓርቲ ህወሓት፣ ሳልሳይ ወያኔ ትግራይ፣ ባይቶና ትግራይና የትግራይ ነጻነት ድርጅት የተባሉት ይገኙበታል።
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ አረና ትግራይ እና የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በክልሉ ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት በሂደቱ ላለመሳተፍ መወሰናቸውን አሳውቀዋል።
ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ፤ ያለው ጊዜ ከአንድ ወር ብዙም ያላለፈ በመሆኑ፤ ከገንዘብና አስፈላጊው አቅርቦት ባሻገር ሌሎችም ዝግጅቶችን ለማከናወን አዳጋች እንደሚሆን እየተገነረ ነው።