ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፈረንሳይ ፖሊሶች የአልጀሪያዊውን አንገት ጠምልለው ለሞት በመዳረግ ክስ ተመሰረተባቸው
በፈረንሳይዋ መዲና ፓሪስ እቃ አድራሽ አልጀሪያዊ መገደሉን ተከትሎ ሶስት ፖሊሶች ክስ ተመስርቶባቸዋል።
የአርባ ሁለት አመቱና የአምስት ልጆች አባቱ ሴድሪክ ቾቪያት ፖሊሶች መሬት ላይ አጣብቀው በያዙት ወቅት ለሰባት ጊዜ ያህል አስጨነቀኝ እያለ ከተማፀነ በኋላ ራሱን ስቷል ተብሏል።
በወቅቱም የሞተር ሳይክል የጭንቅላት መከላከያ አድርጊ የነበረ ሲሆን ለሃያ ሰኮንዶች ያህል መሬት ላይ አጣብቀው እንደያዙትና አቅሉን እንደሳተ የወጣው ቪዲዮ ያሳያል።
ራሱን ከሳተም በኋላ ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ከሁለት ቀናት በኋላ ግለሰቡ ህይወቱ አልፏል።
የአስከሬን ምርመራ እንደሚያሳየው በትንፋሽ ማጠር እንዲሁም ጉሮሮው የሚገኘው አጥንት በመሰበሩ ህይወቱ እንዳለፈ ተጠቁሟል።
ሶስቱ ፖሊሶች ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን በወቅቱ የነበረው አራተኛው ፖሊስ ምርመራ ቢደረግበትም እንዳልተከሰሰ ተገልጿል።
ፖሊሶቹ ግለሰቡን ለሞት ዳርገውታል በሚልም ተከሰዋል።
የሟቹ ቤተሰቦች ለሞት ዳርገውታል የሚል ክስ ውሃ እንደማይቋጥርና ቪዲዮው ላይ እንደሚታየው" በጭካኔ ገድለውታል" የሚል ክስ ሊመሰረትባቸው ይገባል በሚልም እየተከራከሩ ነው።
"ሴድሪክ ቾቪያት መሬት ላይ ስላጋጩትና ስላጣበቁት ነው የሞተው" በማለት ቤተሰቡ በመግለጫው አትቷል። ፖሊሶች በሴድሪክ ላይ የተጠቀሙትን አንገቱን በመጠምለልና መሬት ላይ በመጣል አጣብቀው መጫናቸው እንደገደለውና ይህም ሁኔታ እንዲታገድ የሟች ቤተሰቦች መንግሥትን ጠይቀዋል።
በሰኔ ወር ላይ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ክርስቶፍ ካስታናር ፖሊሶች የሚጠቀሙት አንገትን የመጠምለልና መሬት ላይ የማጣበቅ ሁኔታ ይታገዳል ቢሉም በቀናት ውስጥ የፖሊስ ህብረት ውሳኔውን ቀልብሶታል።
ይህም ሁኔታ የተፈጠረው በርካታ ፖሊሶች በመላው አገሪቷ ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።
ተጠርጣሪዎችን አንገት ጠምልሎ መሬት ላይ መጣል በበርካታ አገሮች ታግዷል።
ሟቹ ተወላጅነቱ ከአልጀሪያ የመጣ ሲሆን በፈረንሳይ ጥቁርና አረብ ወንዶች ከፍተኛ የሆነ የፖሊስ ጭካኔ ተጠቂ ናቸው።
በፈረንሳይ ውስጥም የፖሊስ ጭካኔን በመቃወም በርካቶች ተቃውመው የወጡ ሲሆን በተለይም በጎርጎሳውያኑ 2016 በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለ የሞተው አዳም ቱሬን ተከትሎ በፖሊሶች ላይ ክስ አለመመስረቱ ቁጣን መቀስቀሱ የሚታወስ ነው።
በወቅቱም አንደኛው ፖሊስ አዳም ቱሬን መሬት ላይ ለማጣበቅ ኃይልን መጠቀሙን አምኗል።
በአሜሪካ የጆርጅ ፍሎይድ በነጭ ፖሊስ መገደል ተከትሎም ከፍተኛ የሆነ የፀረ ዘረኝነት ተቃውሞዎች በፈረንሳይ እንዲሁም በመላው አለም ተቀጣጥሏል።