የግሊ ፊልም ተዋናይት ናያ ሪቬራ ከአምስት ቀናት በኋላ አስከሬኗ ተገኘ

ናያ ሪቬራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት ሃይቅ ውስጥ አስከሬን መገኘቱን ተከትሎ ፖሊስ በቅርብ ቀናት ጠፍታ የነበረው የግሊ ፊልም ተዋናይት ናያ ሪቬራ መሆኑን አስታውቋል።

የ33 አመቷ ተዋናይት ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ነበር ከአራት አመት ልጇ ጋር ፒሩ በሚባል ሃይቅ በጀልባ ስትጓዝ ደብዛዋ የጠፋው።

በወቅቱም ልጇ ብቻውን በጀልባ ውስጥ ተኝቶ ተገኝቷል።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችና የባህር ሰርጓጅ ሰራተኞችም ተዋናይቷን ለቀናት ሲፈልጉ ቆይተው በትናንትናው እለት አስከሬኗን አግኝተውታል።

ናያ በታዋቂው ተከታታይ ግሊ በተሰኘው ሙዚቃዊ የቴሌቪዥን ፊልም ሳንታና ሎፔዝ የምትባል ገፀ ባህርይን ወክላ በመጫወት ዝናን አትርፋለች።

በሃይቁ ዳርቻ አስከሬኗ ከተገኘ በኋላ ፖሊስ በሰጠው መግለጫ ወንጀል ተፈፅሞባታል ወይም የራሷን ህይወት አጥፍታለች ብለው እንደማያምኑ አስታውቋል።

የናያ ልጅ ለመዋኘት እንደሄዱና እንዳልተመለሰችም ተናግሯል። ፖሊስ በርካታ ሰዎችን በማሰማራት ተዋናይቷን ለማዳን ፍለጋዎችን ቢያካሂድም ዱካዋ ካለመታየቷ ጋር ተያይዞ አስከሬኗን ወደመፈለግ ተግባር ሄዷል።

የባህር ጠላቂዎችን ጨምሮ፣ የባህር ሰርጓጅ መርከቦች፣የሰለጠኑ ውሾች ሄሊኮፕተርና ሌሎች መሳሪያዎችም ለፍለጋው አገልግሎት መዋላቸው ተገልጿል።

የፖሊስ ቃለ አቀባይ ኬቪን ዶኖግ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ለፍለጋው አስፈላጊ የሚባለውን ግብአት መጠቀማቸውን አስረድተዋል።

ሄሊኮፕተር በመጠቀም ሲፈልጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"በሰላም ነፍስሽን ያሳርፍ፤ እንዴት አይነት ስብዕና የነበረሽ አይት ሰው ነበርሽ። ለቤተሰቦችሽ ፍቅርና ሰላም ይሁንላቸው" በማለት በግሊ ላይ አብራት የምትተውነው ጄን ሊንች በትዊተር ገጿ አስፍራለች

ሌላኛው ተዋናይ ጆሽ ሱስማን በበኩሉ "ናያ በጣም እንናፍቅሻለን" ብሏል

የናያ የተዋናይነት ህይወት የጀመረው ገና በህፃንነቷ ሲሆን በቴሌቪዥን ማስተዋወቂያዎችና ፊልሞች በመተወን እንዲሁም ህፃን ሞዴልም ነበረች።

በአራት አመቷም በተለያዩ የቴሌቪዥን ፊልሞች ላይ ተውናለች። ነገር ግን በአመታት ውስጥ ከሰራችባቸው በግሊ ሙዚቃዊ ፊልም የነበራት ገፀ ባሕርይ ከፍተኛ ተወዳጅነትን አትርፎላታል። በጎርጎሳውያኑ 2014ም ዴቪልስ ዶር በተሰኘው አስፈሪ ፊልምም ተውናለች።

በዚሁ አመት ከተዋናዩ ራያን ዶርሲ ጋር ጋብቻ ፈፅመው አንድ ልጅ አፍርተዋል። ባልና ሚስቱ ከሁለት አመታት በፊት ተፋተዋል።