የፎክስ ኒውስ ታዋቂ ፀሃፊ ዘረኝነትና ፆተኝነትን በሚያንፃባርቅ ፅሁፉ ከስራ ለቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፎክስ ኒውስ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ ያለው ፀሐፊ ዘረኝነትና ፆተኝነት የሚያንፀባርቅ ፅሁፍ በማህበራዊ ሚዲያ መለጠፉን ተከትሎ ከስራ ለቀቀ። ፀሃፊው ለፎክስ የዜና ማዕከል አቅራቢ ተከር ካርልሰንም የሚፅፈው እሱ ነበር።
ከሶስት አመታት በፊት ፎክስ ኒውስን የተቀላቀለው ብሌክ ኔፍ አርብ እለት ነው ከስራ የለቀቀው። ሲኤንኤን ባደረገው ጋዜጣዊ የምርመራ ስራ ብሌክ አውቶ አድሚት በሚባል የበይነ መረብ መወያያ መድረክ ላይ አፀያፊና ዘረኝነት የተሞላባቸው ቃላቶችን ተጠቅሟል ተብሏል። ፎክስ ኒውስ ፅሁፎቹን "ሰቅጣጭና አፀያፊ" ብሏቸዋል።
ብሌክ በነዚህ ፅሁፎች ላይ የብዕር ስሞችን በመጠቀም ጥቁርና እስያዊ አሜሪካውያን ሴቶችን ክብር የሚያዋርድና ከሰውነታቸውም ዝቅ የሚያደርግ ፅሁፎችን አስፍሯል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ጥቁሮችን በሙሉ ወንጀለኞች ናቸው በሚልም አንድ ፅሁፍ ፅፏል። ከዚህም በተጨማሪ በመወያያ መድረኩ ላይ ተሳታፊ የነበረች አንዲት ሴትንም የግል ህይወቷን በማጋለጥ በቃላት ጥቃት አድርሶባታል ተብሏል።
ሲኤንኤን ስለ ብሌክ የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ ባደረገው ምርመራም ቻርለስ በሚል ስም የዘረኝነት ስድብ የሚሳደበው ይኸው ፀሃፊ መሆኑንም ደርሶባታል። ስለ ፀሃፊው የተለያዩ ግላዊ መረጃዎችን በመጠቀምና በማመሳሰል እውነቱንም ደርሶበታል ተብሏል።
አሰሪው ፎክስም በመወያያ መድረኩ ላይ ያሳየው የፀሃፊው ባህርይ በስራው ላይ ታይቶ እንደማይታወቅና የስራ ልልቀቅ ጥያቄውንም ሲያስገባ በፀጋ እንደተቀበሉት አስታውቀዋል።
"መቼም ቢሆን መሳሳት የሌለባችሁ እንዲህ አይነት ተግባር መቼም ቢሆን በድርጅታችን ተቀባይነት የለውም" በማለት ድርጅቱ ገልጿል።
አቅራቢው ተከር ካርልሰንም በዚህ ጉዳይ ላይ ሰኞ መግለጫ ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ወግ አጥባቂ የሚባለው ተከር ፀሓፊው ብሌክን በማሞካሸት "ድንቅ ፀሃፊ" በሚልም ገልፆት ነበር።












