ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኻሾግጂ ግድያ የተጠረጠሩ 20 የሳዑዲ ዜጎች በሌሉበት ጉዳያቸው ቱርክ ውስጥ ሊታይ ነው
ሃያ የሳኡዲ አረቢያ ዜጎች ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂን በመግደል ተጠርጥረው በሌሉበት ቱርክ ውስጥ ጉዳያቸው ሊታይ ነው።
ጋዜጠኛ ኻሾግጂ የተገደለው እኤአ በ2018 ጥቅምት ወር ቱርክ በሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ውስጥ ነበር።
ሁለት የቀድሞው የልዑል ሞሐመድ ቢን ሰልማን የቅርብ ረዳቶች በኻሾግጂ ግድያ ተጠርጥረው በሌሉበት ጉዳያቸው ከሚታየው 20 ሳኡዲዎች መካከል እንደሚገኙበት ተገልጿል።
ሳኡዲ አረቢያዊው ጃማል ኻሾግጂ ከአገሩ ተሰዶ አሜሪካ ውስጥ ይኖር የነበረ ሲሆን ልዑሉ ለውጥ እንዲያመጡ በሥራው ይወተውት የነበረ ግለሰብ ነበር።
ሳኡዲ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተሟላ አይደለም ተብሎ ቢተችም ከጋዜጠኛው ግድያ ጋር በተያያዘ የራሷን ችሎት አካሂዳለች።
በኢስታንቡል የሚካሄደው ይህ ችሎት የዓለም አቀፉ ማኅረበረሰብ ጩኸትን ተከትሎ የመጣ ነው።
የቱርክ አቃቢያነ ሕጎች የኻሾግጂን ግድያ በማዘዝና በማስፈፀም የቀድሞውን የሳኡዲ ደኅንነት ምክትል ኃላፊ፣ አህመድ አል አሲሪ፣ እና የንጉሣውያን ችሎት ሚዲያ አማካሪ ሳዑድ አል ቃሃትኒን ወንጅለዋል።
ቀሪዎቹ 18 ተከሳሾች ኻሾግጂን በማፈን እና በመግደል የተከሰሱ ናቸው። የኻሾግጂ አስከሬን ያልተገኘ ሲሆን የቱርክ ባለስልጣናት በቆንስላው ውስጥ የተገደለው ኻሾግጂ፣ ወደ ቅጥር ግቢው እንደገባ ነበር የታነቀው በማለት በወቅቱ መግለጫ ሰጥተው ነበር።
ከዚያም የጋዜጠኛው አካል ተቆራርጦ እንዲጠፋ ተደርጓል ስትል ቱርክ ሳኡዲን ትከሳለች።
ጋዜጠኛው አሜሪካ የሚኖር ቢሆንም ወደ ቆንስላው የገባው ለሠርጉ የሚያስፈልገውን ወረቀት ለማግኘት ነበር።
የጋዜጠኛው እጮኛ የነበረችው ሃቲስ ሴንጊዝ ከተባበሩት መንግሥታት የህገወጥ ግድያዎች ልዩ መልዕክተኛ፣ አግነስ ካላማርድ ጋር በመሆን ችሎቱን እንደምትከታተል የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የሳኡዲ ባለስልጣናት መጀመሪያ ላይ እጃችን የለበትም ብለው ቢክዱም በኋላ ግን "በአግባቡ ያልተከናወነ ኦፕሬሽን ነው" ብላ ነበር።
በሕዳር ወር በሳኡዲ አረብያ ጉዳዩን የተከታተለው ችሎት አምስት ሰዎችን በሞት ሦስት ሰዎችን ደግሞ በእስር የቀጣ ሲሆን ነገር ግን ችሎቱ ሚስጥራዊ የነበረ በመሆኑ ተከሳሾቹም እነማን እንደሆኑ አልተገለፀም።