ሩሲያ በአፍጋኒስታን የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮችን ለታጣቂዎች ገንዘብ በመክፈል አስገድላለች መባሏን ካደች

የአሜሪካ ወታደሮች በአፍጋኒስታን
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ሩሲያ ከሰሞኑ በአፍጋኒስታን የሰፈሩ የአሜሪካና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን አገሮች ድርጅት (ኔቶ) ወታደሮችን ከታሊባን ግንኙነት ባላቸው ታጣቂዎች ገንዘብ ከፍላ አስገድላለች የሚባለው መሰረት የሌለው ውንጀላ ነው በማለት ክዳለች።

ኒውዮርክ ታይምስና ዋሽንግተን ፖስት የአሜሪካ ባለስልጣናትን ዋቢ አድርገው እንደዘገቡት በአውሮፓ ከተቃጣው የግድያ ሙከራዎች ጋር ግንኙነት አለው የተባለ የሩሲያ ወታደራዊ ደህንነት ክፍል ኢላማ የነበሩ ሰዎችን ስም ዝርዝር ባለፈው ሰጥቷል ተብሏል።

በአሜሪካ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ በበኩሉ እንዲህ አይነት ውንጀላዎች ፍፁም ሃሰት ነው በማለት ያጣጠለ ሲሆን ለዲፕሎማቶችም ስጋት ፈጥሯል ብሏል።

ታሊባንም በበኩሉ ከሩሲያ ደህንነት ጋር እንዲህ አይነት ስምምነት አልተደረሰም በሚል ክዷል።

አሜሪካ ባሁኑ ሰዓት በአፍጋኒስታን ያደረገችውን የ19 አመት ጦርነት በማቆም የሰላም ስምምነት ለማድረግ ሙከራ ላይ ናት።

ኒውዮርክ ታይምስ ጨምሮም መጋቢት ወር ላይ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስለዚህ ሪፖርት ተነግሯቸው የነበረ መሆኑን ቢዘግብም ዋይት ሃውስ ክዷል።

"ፕሬዚዳንቱም ሆነ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ስለተባለው የሩሲያ ደህንንት ኢላማ ስላደረጋቸው ሰዎች የሰሙት ነገር የለም" በማለት የዋይት ሃውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካይሌይግ ማክኤናኒ በትናንትናው ዕለት ተናግረዋል።

ፕሬስ ሴክሬታሪዋ አክለውም የሩሲያ ደህንነት ኢላማ ስላደረጋቸው ሰዎች ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሰምተዋል ብሎ ኒውዮርክ ታይምስ መዘገቡ ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ ነው ብለዋል።

ስማቸው ያልተጠቀሰው ባለስልጣናት ለኒውዮርክ ታይምስ እንደተናገሩት የሩሲያ ደህንነት ክፍል የጥምር ኃይሉን የሚመሩ ሰዎችን በማስወገድ ተልዕኮውን ለማፈራረስ አቅዷል የሚል መደምደሚያ ላይ የአሜሪካ ደህንነት መድረሱን ነው።

ጋዜጣው አክሎም ከታሊባን ጋር ግንኙነት የነበራቸው ታጣቂዎች ለዚህ እንደተመለመሉና ገንዘብም ተቀብለዋል ብሎ ዘግቧል።

በአሜሪካ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲም ሃሰተኛ ዜና ነው በሚል በተከታታይ ባወጣቸው የትዊተር ፖስቶች አስፍሯል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

በጎርጎሳውያኑ 2019 ሃያ የሚሆኑ የአሜሪካ ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን ኒውዮርክ ታይምስ የትኞቹን ግድያዎች እንደጠረጠራቸው ግልፅ አላደረገም።

በኒውዮርክ ታይምስ ዋቢ የተደረጉት ባለስልጣናት አክሎም እንደገለፁት የዋይት ሃውስ ብሔራዊ የፀጥታ ጉባኤ ለዚህም ምን አይነት ምላሽ እንደሚሰጥ እየመከረ የነበረ ሲሆን በሩሲያም ላይ ማዕቀብንም እንዳሰበ ተገልጿል።

የታሊባን ቃለ አቀባይ ውንጀላውን መሰረተ ቢስ ሲሉ አጣጥለውታል።

"በኢላማ የምንገድላቸውም ሆነ ግድያዎቹ ለአመታት የቀጠሉ ናቸው፤ ያለማንም ድጋፍ በራሳችንም አከናውነናቸዋል" በማለት ዛቢሁላህ ሙጃሂድ ለኒውዮርክ ታይምስ ተናግረዋል።

ቃለአቀባዩ አክለውም የአሜሪካና የኔቶ ወታደሮችን የካቲት ላይ ጦራቸውን ለማስወጣት እንዲሁም ማዕቀቡን ለማንሳት ከተስማሙ በኋላ ጥቃት ማድረስ እንዳቆሙ ተናግረዋል። በምላሹም ታሊባን በሚቆጣጠሯቸው ግዛቶች ፅንፈኛ ቡድኖች እንዳይንቀሳቀሱ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የሩሲያ ደህንነት ክፍል የቀድሞ የሩሲያ ጥምር ሰላይ የነበረውን ሰርጌይ ስክሪፓልና ልጃቸው ዩሊያናንም በእንግሊዝ በጎርጎሳውያኑ 2018 በመግደልም ይጠረጠራል።