በደቡብ ኮሪያ ኮሮናቫይረስ ለሁለተኛ ዙር ሳያገረሽ አይቀርም ተባለ

የህክምና ባለሙያዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ምንም እንኳን በበሽታው ተይዘው የተገኙ የህሙማን ቁጥር ዝቅተኛ ቢሆንም የደቡብ ኮሪያ የጤና ባለስልጣናት ወረርሸኙ ማገርሸቱን እንደሚያምኑ ገለጹ።

ደቡብ ኮሪያ የኮሮናቫይረስን በመቆጣጠር በኩል ተሳክቶላታል ተብሎ ሲነገር የነበረ ቢሆንም አሁን እያንሰራራ ያለውን በሽታ ለመቆጣጠር ወራት ሊያስፈልጋት እንሚችል እየተነገረ ነው።

የኮሪያ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከላት ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ጂዮንግ ኢዩን-ኪዮንግ እንዳሉት የመጀመሪያው ዙር የወረርሽኙ ክስተት እስከ ሚያዚያ ወር ማብቂያ ድረስ ቆይቶ ነበር።

ነገር ግን ከግንቦት ወር ጀምሮ በዋና ከተማዋ ሴኡል ውስጥ የሚገኝን የምሽት ክበብን ጨምሮ በአንዳንድ ስፍራዎች ላይ በሽታው ተከስቷል።

በሽታው በቁጥጥር ስር ውሏል በተባለበት ጊዜ በየዕለቱ ይመዘገብ የነበረው ወደ አንድ ሺህ የሚጠጋ የአዲስ ህሙማን ቁጥር ለተከታታይ ሦስት ቀናት ዜሮ ሆኖ ቆይቷል።

ዛሬ ባለስልጣንት እንዳስታወቁት ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ከፍተኛ የተባለው 17 አዲስ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች በተለያዩ ቢሮዎችና መጋዘኖች አካባቢ መገኘታቸው ታውቋል።

ኃላፊዋ የወረርሽኙ መልሶ ማገርሸት አገሪቱ ወደ ሁለተኛ ዙር የቫይረሱ ወረራ እየገባች መሆኑን የሚያመለክት ሳይሆን እንደማይቀር ገልጸው፤ ይህም ለወራት ሊቆይ እንደሚችል ስጋታቸውን ተናግረዋል።

ዛሬ ጠዋት ከዋና ከተማዋ በስተደቡብ የምትገኘውና ከትልልቅ የአገሪቱ ከተሞች መካከል አንዷ የሆነችው ዴጆን በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በበሽታው ተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን ተከትከሎ በሙዚየሞችና በቤተ መጽሐፍት ውስጥ መሰብሰብን ከልክላለች።

የዋና ከተማዋ ሴኡል ከንቲባም በሚቀጥሉት ሦስት ቀናት በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 30 ከደረሰና በከተማዋ ባሉ ሆስፒታሎች ከሚገኙ አልጋዎች መካከል የሚያዘው ከ70 በመቶ ከበለጠ ቀደም ሲል ተጥሎ የነበረው ጥብቅ ማኅበራዊ ርቀትን የመጠበቅ ግዴታ ተመልሶ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ደቡብ ኮሪያ በአገሪቷ ውስጥ የመንቀሳቀስ እገዳ ሳትጥል ሕዝቡ በፈቃደኝነት ማኅበራዊ ርቀትን የመጠበቅ እርምጃን ሲወስድ መንግሥት ደግሞ በሽታው ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ፣ በመመርምርና በመለየት የተሳካ የመቆጣጠር ሥራ ተከናውኗል።

ደቡብ ኮሪያ በሽታው በግዛቷ ውስጥ መገኘቱን ሪፖርት ካደረገችበት ከጥር ወር መጀመሪያ ወዲህ በአጠቃላይ 280 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸው ታውቋል።

በአገሪቱ እስካሁን ድረስ በአጠቃላይ ከ12 ሺህ በላይ ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸው የተመዘገበ ሲሆን አብዛኞቹ አገግመው በክትትል ላይ የሚገኙት 1,277 ብቻ መሆናቸው ተነግሯል።