በኮሪያ ሙዚቀኞች ሰበብ የተመናመነው የትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ

የትራምፕ ደጋፊዎቸ በተልሳ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ፕሬዝደንት ትራምፕ ኦክላሆማን በአንድ እግሯ ለማቆም ሲዝቱ ነው የሰነበቱት። የምርጫ ቅስቀሳ ምን እንደሚመስል አሳያችኋለሁ ሲሉም ፎክረዋል። ነገር ግን እሳቸው ያሰቡት ወዲህ እውነታው ወዲያ ሆነባቸው።

ትራምፕ አሜሪካን ለሁለተኛ ክፍለ-ጊዜ ለመምራት ቅስቀሳ ጀምረዋል። አሜሪካን ታላቅ አደርጋለሁ ከሚለው መፈክራቸው የአሜሪካን ታላቅነት አስቀጥላለሁ ወደሚል ተሻግረዋል።

ኦክላሆማ ግዛት፤ ተልሳ ከተማ ውስጥም ይህን ታሪክ በቀይ እፅፋለሁ ሲሉ መፎከር ከጀመሩ ሳምንታት ተቆጥረዋል።

ልክ ሰዓቱ ደርሶ የትራምፕ ደጋፊዎች አዳራሹን ከአፍ እስከገደፉ ይሞሉታል ተብሎ ሲጠበቅ ግን ትራምፕ ያሰቡት ሳይሆን ጠላቶቻቸውን ያስፈገገ ታሪክ ተሰራ።

ይህን ያስተዋሉ የትራምፕ ነቃፊዎች በየማሕበራዊ ድር-አምባዎቻቸው እየወጡ ሰውዬውን መዘባበቻ አደረጓቸው። የኮሪያ ሙዚቀኞችንም ያመሰግኑ ጀመር።

ትራምፕና የኮሪያ ሙዚቀኞች ደግሞ ምን አገናኛቸው? ጥሩ ጥያቄ ነው።

ነገሩ ወዲህ ነው። ኬፖፕ የተሰኘው የኮሪያ ሙዚቃ ዘውግ አሜሪካ ውስጥ ዝናው የናኘ ነው። ታዲያ እኒህ የኮሪያ ሙዚቀኞች ቲክ-ቶክ በተሰኘው ማሕበራዊ ድር-አምባ ለደጋፊዎቻቸው አንድ መልዕክት ይልካሉ። 'የትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ ላይ እንሳተፋለን ብላችሁ ቲኬት ያዙ፤ በቅስቀሳው ላይ ግን እንዳትገኙ' የሚል።

የትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ ሰዎች ይህ ሃሰት ነው ሲሉ ይከራከራሉ።

አዳራሹ 19 ሺህ ሰው አቅፎ ደግፎ ይይዛል። የቅስቀሳው ሰዎች አዳራሹ መሙላቱ ስለማይቀር ከአዳራሹ ውጭ ያለውን ቦታ እንጠቀማለን የሚል ዕቅድ ነበራቸው።

የተልሳ ከተማ እሳት አደጋ ሰዎች ብርጌድ ለቅስቀሳው የተገኙ ሰዎች ቁጥር ከ6 ሺህ አይበልጥም ሲሉ ተሰምቷል። የትራምፕ ሰዎች ግን ቁጥሩ ከዚያ በጣም ይልቃል ሲሉ ይሞግታሉ።

የቅስቀሳ ኃላፊ ብራድ ፓርስካል እኛ ሰዎች ቲኬት ገዝተው ይቀራሉ የሚል እሳቤ የለንም፤ ምክንያቱም ወደ አዳራሹ ቀድሞ የመጣ መግባት ይፈቅደልታልና ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።

"መገናኛ ብዙሃንና እና ተቃዋሚዎች ሰዎች ወደ ቅስቀሳው እንዳይሄዱ አድርገዋል" ሲሉም ወቅሰዋል።

"ግራ ዘመሞች ቅስቀሳ እንዴት እንደሚከናወን አያውቁም። ሰዎች ቅስቀሳውን ለመታደም ሲመዘገቡ ስልክ ቁጥራቸውን እንመዝባለን፤ መገኘት መቻላቸውንም እናረጋግጣለን። ይህን የምናደርገው ሃሰተኛ ተመዝጋቢዎችን ለመመንጠር ነው።"

የሪፐብሊካን ፓርቲ አባል የነበሩትና የትራምፕ ዋነኛ ነቃፊ የሆኑት ስትቭ ሽሚድት የ16 ዓመት ልጃቸውንና ጓደኞቿን ጨምሮ በርካታ ታዳጊ አሜሪካውያን ቲኬት ጠይቀው ነገር ግን ቅስቀሳውን አልታደሙም ሲሉ በትዊተር ግድግዳቸው ላይ ፅፈዋል።

በርካታ ወላጆችም 'አዎ ልጆቻችን እንዲህ አድርገዋል' ሲሉ እየተደመጡ ነው።

ወጣቷ ፖለቲከኛ አሌክሳንደር ኦስካዚዮ ኮርቴዝ ወጣቶችና የኬ-ፖፕ ለዚህ ድርጊታቸው አድናቂዎችን አንቆለጳጵሰዋል።

ወጣቶቹ ምን ያክል ቲኬቶችን ሸምተን እንገኛለን ብለው እንደቆረጡ በውል የታወቀ ቁጥር ባይኖርም ከቀናት በፊት ቲክ ቶክ የተሰኘው ድር ላይ ታዳጊዎች ይህን እንዲያደርጉ ሲሰብክ የነበረ ወጣት 700 ሺህ 'ላይኮች' አግኝቷል።

ትራምፕ፤ መጀመሪያ ቅስቀሳውን ማድረግ አስበው የነበረው በግሪጎሪ አቆጣጠር ሰኔ 19 ነበር። ይህ ቀን ደግሞ ጁንቲንዝ ይባላል። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ባርነት ሕገ-ወጥ እንዲሆን የተወሰነበት ነው።

ትራምፕ በዚህ ቀን ቅስቀሳ ላካሂድ ማለታቸው ብዙዎችን አስከፍቶ ነበር። አልፎም ቅስቀሳው በአሜሪካ ታሪክ አስከፊው የዘር ጭፍጨፋ የተካሄደባት ተልሳ ውስጥ መሆኑ ቁጣን መጫሩ አልቀረም።

ከዚህ በኋላ ነው የቅስቀሳው ቅዳሜ ሰኔ 20 እንዲሆን የተደረገው።

ቅስቀሳው ላይ የተገኘው የቢቢሲው አንተኒ ዙርከር ምንም እንኳ ቲኬቶችን የቆረጡ ሰዎች ባይገኙም የትራምፕ ደጋፊዎች ቢመጡም ቦታ አያጡም ነበር ሲል ዘግቧል። ነገር ግን በርካታ ቲኪቶች መያዛቸው ደጋፊዎችን ሳያዘነጋ አልቀረም ይላል።

ቅስቀሳው ላይ የተገኙ ሰዎች ቁጥር የተመናመነ መሆኑ ሲታወቅ ወጣቶችን ሲቀሰቅስ የነበረው ግለሰብ በተለይ ደግሞ ዕድሜያቸው ለምርጫ ያልደረሰ ታደጊዎችን ሲያመሰግንና ሲያደንቅ ታይቷል።

የኬ-ፖፕ ሙዚቃ አድናቂዎች ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ሲያመጡ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።

በቅርቡ አሜሪካን በተቃውሞ የናጣት የጆርጅ ፍሎይድ ግድያን ተከትሎ ብላክ ላይቭስ ማተር [የጥቁሮች ሕይወት ዋጋ አላት] ለተሰኘው ተቋም በርካታ ገንዘብ ማሰባሰብ ችለዋል።

ኮሮናቫይረስ

ቅስቀሳውን የሚታደሙ ሰዎች ለኮሮናቫይረስ ቢጋለጡ የትራምፕ ቅስቀሳ ቡድን ተጠያቂ እንደማይሆን የሚያትት ቅፅ ፈርመው ነው ወደ አዳራሹ የገቡት።

ቅስቀሳው ሊጀምር ሰዓታት ሲቀሩት ከአስተባባሪዎች መካከል 6 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተነግሮ ነበር።

አብዛኛዎች የትራምፕ ደጋፊዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አልጣለቁም።

የሪፐብሊካኖች ግዛት በሆነችው ኦክላሆማ ሁለት ሰዓት ገደማ የፈጀ ንግግር ያደረጉት ትራምፕ በርካታ ጉዳዮችን ሲያነሱ ሲጥሉ አምሽተዋል።

ቅስቀሳው በዚህ የወረርሽኝ ወቅት እንዳይካሄድ ብዙዎች ቢወተውቱም ትራምፕ ሊሰሟቸው ፈቃደኛ አልነበሩም።

አሜሪካ 2.2 ሚሊዮን ሰዎች በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተይዘውባታል። 119 ሺህ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል።