በእንግሊዝ የሽብር ድርጊት ነው በተባለ የስለት ጥቃት አንድ ግለሰብ ሦስት ሰዎችን ገደለ

ታትሟል

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ሬዲንግ በምትባል ከተማ ባለ መናፈሻ ውስጥ አንድ ግለሰብ በስለት በፈጸመው ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ ሌላ ሦስት ሰዎች ደግሞ ክፉኛ መቁሰላቸው ተረጋገጠ።

ጥቃቱን ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረው ግለሰብ በመናፈሻው ውስጥ የተያዘ ሲሆን ፖሊስ ግለሰቡ የ25 ዓመቱ ሊቢያዊ ኻይሪ ሳዳላህ እንደሚባል አሳውቋል።

የስለት ጥቃቱ የተፈጸመው ትናንት [ቅዳሜ] አመሻሽ ላይ ሲሆን በርካታ ሰዎች በስለት ተወግተዋል።

መጀመሪያ ላይ ፖሊስ ድርጊቱ ከሽብር ተግባር ጋር የተያያዘ ነው ባይልም የጸረ ሽብርተኝነት መርማሪዎች ወደ ስፍራው ተጠርተዋል ምርመራ አድርገዋል።

በዚህም ጥቃቱ ከሽብር ድርጊት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ፖሊስ ገልጾ ቀጣይ ሥራውንም ከሽብር ድርጊት ጋር አያይዞ እንደሚያከናውን አስታውቋል።

የወንጀሉ መርማሪ ፖሊስ ኢያን ሃንተር እንዳሉት በቁጥጥር ስር ከዋለው ተጠርጣሪ ውጪ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ፖሊስ ተጨማሪ ተጠርጣሪ እየፈለገ አይደለም።

ጨምረውም "እስካሁን ጥቃቱን እንደሽብር ድርጊት አልያዝነውም ነገር ግን ፖሊስ ምክንያቱን ለማወቅ ከጸረ ሽብር ድርጊት መርማሪዎች ጋር እየሰራን ነው" ብለዋል።

ፖሊስ ጥቃቱ ሲፈጸም ድርጊቱን በሞባይል ቪዲዮ የቀረጸ ካለ መረጃውን እንዲሰጠው ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፤ ለጥቃቱ ሰለባ ቤተሰቦች ክብር ሲባል ምስሎችን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እንዳይሰራጩ ጠይቋል።

አንድ በስፍራው የነበረ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ እንደተናገረው ጥቃት ፈጻሚው በመናፈጻው ውስጥ ተሰብስበው በነበሩ ሰዎች መካከል እየተንቀሳቀሰ ሰዎችን በስለት ለመውጋት እንደሞከረና ወደ እሱም እየሮጠ መምጣቱን ገልጿል።

ሰንደይ ሚረር የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው በሰዎች ላይ በስለት ጉዳት ያደረሰውን ግለሰብ አንድ ፖሊስ ታግሎ ከመሬት ላይ ከጣለው በኋላ በቁጥጥር ስር ውሏል።