ኮሮናቫይረስ በይፋ ከተነገረበት ከወራት በፊት መከሰቱ ጥናቶች አመለከቱ

የጣሊያን ሳይንቲስቶች በአገሪቱ የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ ህመምተኛ ከመገኘቱ ከወራት በፊት በሁለት ከተሞች ውስጥ በሚገኙ የፍሳሽ መስመሮች ውሃ ውስጥ የቫይረሱ ምልክቶች መገኘታቸውን ገለጹ።
የጣሊያን ብሔራዊ የጤና ተቋም በሚላንና በቱሪን ከተሞች ውስጥ በውሃ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ምልክቶችን በታህሳስ ወር ላይ መገኘቱን አሳውቋል።
ይህም በሌሎች አገራት እየተባለ እንዳለው በሽታው ከሚታሰበው ጊዜ ቀደም ብሎ ሲሰራጭ ነበረ ለሚለው መላምት ማስረጃ ይሆናል እየተባለ ነው።
የቻይና ባለስልጣናት በአገራቸው በሽታው ስለመከሰቱ ያረጋገጡበት የመጀመሪያውን ታማሚ ያገኙት በታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ ነበረ። በጣሊያን ደግሞ በሽታው መገኘቱ የተረጋገጠው በየካቲት ወር አጋማሽ ላይ ነበረ።
በፈረንሳይ ውስጥ በግንቦት ወር ከፓሪስ አቅራቢያ ከመጣ በሳምባ ምች የተጠረጠረን ታማሚ ናሙና ላይ ምርመራ ቢደረግም በቫይረሱ ተይዟል ተብሎ የሚታመነው ግን በኅዳር ወር ላይ ነበረ።
ስፔን ውስጥም የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው ባርሴሎና ውስጥ በፍሳሽ መስመሮች ውሃ ላይ በጥር ወር ላይ ምርመራ ተደርጎ የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ተገኝተው ነበር። ይህ ማለትም የመጀመሪያ የወረርሽኙ ታማሚ መገኘቱ ከመረጋገጡ ከ40 ቀናት በፊት መሆኑ ነው።
የጣሊያን ተመራማሪዎች በሰሜናዊ ጣሊያን ከሚገኙ 40 የቆሻሻ ውሃ ማጣሪያ ጣቢያዎች ከጥቅምት እስከ የካቲት ድረስ በተሰባሰቡ የውሃ ናሙናዎች ላይ ምርመራ አድርገዋል።
በጥቅምትና ኅዳር የተሰበሰቡት ናሙናዎች ላይ የቫይረሱ ምልክቶች አለመገኘታቸው ሲረጋገጥ በዚህም በሽታው በወቅቱ በአካባቢው እንዳልነበረ የጣሊያኑ የጤና ምርምር ተቋም ባለሙያ ጁሴፒና ላ ሮሳ ገልጸዋል።
ከቦሎኛ የተገኘው የቆሻሻ ውሃ ናሙና ግን በጥር ወር ላይ የኮሮናቫይረስ ምልክቶችን ማሳየት እንደጀመሩ ተነግሯል።
እነዚህ ግኝቶች ተመራማሪዎች ቫይረሱ ጣሊያን ውስጥ እንዴት እንደተነሳና እንደተሰራጨ ለመረዳት እድል ይፈጥርላቸዋል ብለዋል ላ ሮሳ።
በጣሊያን የመጀመሪያው በአገር ውስጥ በቫይረሱ እንደተያዘ የተረጋገጠው ሰው የተገኘው በሎምባርዲ ክልል ውስጥ በምትገኘው ኮዶኛ ከተማ ውስጥ ነበር።
ከተማዋ ከየካቲት ወር አጋማሽ አንስቶ እንድትዘጋ ተደርጋ "የአደጋ ክልል" ስትባል፤ መጋቢት ላይ ደግሞ በዙሪያዋ ያሉ ዘጠኝ ከተሞች በተመሳሳይ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎባቸው ነበር።
ከፍሳሽ መስመሮች በተሰበሰቡ ናሙናዎች ላይ በተደረገው ምርመራ በሽታው በሰዎች ላይ መገኘቱ ከመረጋገጡ ከወራት ቀደም ብሎ የቫይረሱ ምልክቶች እንደነበሩ መታወቁ፤ ወረርሽኙ መከሰቱ በይፋ ከመታወቁ ቀደም ብሎ እንደነበር እያመለከተ ነው። በርካታ አገራትም ይህንን ዘዴ በመጠቀም ምርመራ ማድረግ ጀምረዋል።
የጣሊያን ብሔራዊ የጤና ተቋም ከዚህ በተጨማሪ ቱሪስቶች በሚያዘወትሯቸው ቦታዎች ላይ ከሐምሌ ጀምሮ በተሰበሰቡ የፍሳሽ ናሙናዎች ላይ ምርመራ ለመጀመር አቅዷል።
በጣሊያን ውስጥ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከ40 ሺህ ሰዎች በላይ ህይወታቸውን አጥተዋል።












