በኢትዮጵያ ዴክሳሜታዞን ጥቅም ላይ እንዲውል ተወሰነ

ታትሟል

በቅርቡ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በጽኑ ታምመው ለሚገኙ ሰዎች ተሰጥቶ ውጤት ማሳየቱ የተገለጸው ዴክሳሜታዞን የተባለው መድኃኒት በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲወል ተወሰነ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ፌስቡካቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት እንዳስታወቁት በዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በዴክሳሜታዞን የተባለውን መድኃኒት ለኮቪድ-19 ህሙማን ለመጠቀም የተደረገውን ጥናትና ሪፖርቱን በዝርዝር መስሪያ ቤታቸው እንደተመለከተው ገልጸዋል።

ጨምረውም የሚኒስቴሩ የህክምና ጉዳዮች አማካሪ ቡድንና የጤና ባለሙያዎች አማካሪ ምክር ቤት ያቀረበውን ምክረ ሀሳብ መሰረት በማድረግ ጥቅም ላይ እንዲውል መወሰኑን አመልክተዋል።

በዚህም "ዴክሳሜታዞን ኦክሲጅን ወይም የመተንፈሻ መሳሪያ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው የኮቪድ-19 ህሙማን የህክምና ባለሙያዎች በሚያዙት መሰረት እንደ ድንገተኛ ህክምና ለመጠቀም ተወስኗል" ብለዋል።

በተጨማሪም በዚህ መድኃኒት የሚሰጠውን ህክምና አስመልክቶ በባለሙያዎች የሚዘጋጅ ዝርዝር መመሪያ በቅርቡ እንደሚወጣ የጤና ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በሙከራ ወቅት የኮሮናቫይረስ ጽኑ ህሙማን ላይ ባሳየው ውጤት መሰረት ይህን መድኃኒት የዓለም የጤና ድርጅት እንደተቀበለው ከቀናት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል።

በሙከራው ላይ ዴክሳሜታዞን በኮሮናቫይረስ በጽኑ ከታመሙ ሰዎች መካከል የአንድ ሦስተኛውን ሕይወት መታደግ እንደሚችል እና በወረርሽኙ ሰበብ ኦክስጂን በሚያስፈልጋቸው ሰዎች ላይ የሚያጋጥምን ሞት ደግሞ በአንድ አምስተኛ ሊቀንስ እንደሚችል ለድርጅቱ የቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ ግኝት ማመልከቱ ተገልጿል።

ዴክሳሜታዞን ከ1960ዎቹ (እአአ) ጀምሮ በተለያዩ ህመሞች ምክንያት የሚያጋጥሙ እብጠቶችን ለመቀነስና የተወሰኑ አይነት የካንስር ህመሞችን ለማከም ጥቅም ሲውል ቆይቷል።

በርካሽ ዋጋና በስፋት የሚገኘው ዴክሳሜታዞን በኮቪድ-19 በጽኑ የታመሙ ሰዎች ሕይወት አድን መሆኑ መነጋገሪያ ሆኗል።

ይህ መድኃኒት የኮሮናቫይረስን የመከላከልም ሆነ የመፈወስ የታወቀ ውጤት እንደሌለው ባለሙያዎች የገለጹ ሲሆን አስፈላጊነቱም በሐኪሞች ሲወሰን በጸና ለታመሙ ሰዎች ብቻ የሚሰጥ ነው።

በጤና ሚኒስቴር የህክምና ግልጋሎት ዋና ኃላፊ የሆኑት አቶ ያዕቆብ ሰማን ለቢቢሲ እንደተናገሩት በአንዳንድ ሰዎች ተጋንኖ እንደሚነገረው ሳይሆን የመድኃኒቱ ፋይዳ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ በፅኑ ሕክምና ላይ የሚገኙ ህሙማንን የሞት መጠን መቀነስ እንደሆነ፣ ይህ አዎንታዊ ጠቀሜታውም በቁጥር ደረጃ ሲሰላ አነስተኛ ነው ብለዋል።

ከበሽታው እራስን ከመጠበቅ አንጻርም "በማኅበረሰቡ ዘንድ መዘናጋትን እንዳይፈጠር አሁንም ዋነኛው መተኮር ያለበት መንገድ ባለሞያዎች የሚሰጡት የመከላከያ እርምጃዎች ተግባራዊ መድረግ ነው" ብለዋል አቶ ያዕቆብ ሰማን።