በሜደትራኒያን ባህር በርካታ ስደተኞች ሰጥመው ሞቱ

ከአራት ዓመት በፊት እየሰጠመች ካለች ጀልባ የጣሊያን ባህር ኃይል ስደተኞችን ሲታደግ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

የምስሉ መግለጫ, ከአራት ዓመት በፊት እየሰጠመች ካለች ጀልባ የጣሊያን ባህር ኃይል ስደተኞችን ሲታደግ
ታትሟል

በሜደትራኒያን ባህር በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች ሰጥመው ሞቱ።

ስደተኞችን ጭና የነበረች ጀልባ ከሰጠመች በኋላ የ46 ስደተኞች አስክሬን መገኘቱን የቱኒዚያ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

ስደተኞቹን የጫነችው ጀልባ የሰጠመችው ሳፋክስ ተብላ በምትጠራ የቱኒዚያ ከተማ አቅራቢያ ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ ነው። የአከባቢው ባለስልጣናት እንዳሉት አሁንም ቢሆን ከ46ቱ ሰዎች በተጨማሪ በአደጋው ህይወታቸውን ያጡ ስደተኞች ስለሚኖሩ አስከክሬን አሰሳ ላይ ናቸው።

ጣሊያን ለመድረስ ጉዞ ጀምረው ጀልባቸው ከሰጠመች በኋላ ህይወታቸው ያለፉ ስደተኞች ዜግነት ባለስልጣናት ባያሳውቁም፤ የቱኒዚያ መንግሥት ዜና ወኪል የሆነው ቲኤፒ፤ አብዛኛዎቹ ሟቾች የአይቮሪ ኮስት ዜጎች ናቸው ሲል ዘግቧል።

አስክሬናቸው ከተገኙ ስደተኞች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች ናቸው። ከሟቾቹ መካከል አንዱ ቱኒዚያዊ መሆኑ በፖሊስ የተረጋገጠ ሲሆን፤ ምናልባት ጀልባዋን ሲያሽከረክር የነበረው እሱ ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል።

የቱኒዚያ ፍርድ ቤት በርካቶች ህይወታቸውን ካጡበት አደገኛ የጀልባ ጉዞ በስተጀርባ ያሉ አካላት እነማን እንደሆኑ ፖሊስ እንዲመረምር ሲል መወሰኑም ተሰምቷል።