ኮሮናቫይረስ፡ ቢሊየነሩ ቢል ጌትስን ለሴራ ትንተና ያጋለጣቸው ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከአምስት ዓመት በፊት ቫንኩቨር የተካሄደው ‘ቴድ’ (TED) መድረክ ላይ ተናገሪ የነበሩት ቢልየነሩ ቢል ጌትስ ነበሩ።
“በቀጣጥ አስርት ዓመታት ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የሚገድለው ጦርነት ሳይሆን ተላላፊ ቫይረስ ነው” ብለው ተናግረዋል።
የዚያን መድረክ ንግግራቸውን ቢቢሲን ጨምሮ ብዙዎች ሽፋን ቢሰጡትም፤ ተገቢው ትኩረት አልተቸረውም ነበር።
ኮቪድ-19 መሰራጨት ከጀመረ በኋላ በርካቶች ንግግሩን ወደኋላ ተመልሰው እያዳመጡት ነው። ከ64 ሚሊዮን ጊዜ በላይ የንግግሩ ቪድዮ ታይቷል።
ብዙዎች ከንግግሩ ጀርባ ምን እንዳለ ለማወቅ ይፈልጋሉ። አንዳንዶች ‘የዓለም ምሁራንን በአንዳች አቅጣጫ እየመራ ነው’ ይሏቸዋል። ‘የዓለምን የሕዝብ ቁጥር ለመቀነስ ይፈልጋል’ ሰሉ የሚወነጅሏቸው አልታጡም። ክትባትን አስገዳጅ በማድረግ በሰው ልጆች ሰውነት ማይክሮቺፕ ይቀብራሉ ተብሎም ተወርቷል።
በርካታ የሴራ ትንተናዎች ስለ ቢል ጌትስ
“ስለ ቢል ጌትስ በሺዎች የሚቆጠሩ የሴራ ትንታኔዎች አሉ። የእያንዳንዱ ማኅበረሰብ የሴራ ትንተና የሚያጠነጥነው በእሱ ዙርያ ነው። ከሕብረተሰብ ጤና ጋር በተያያዘ ብዙ ስለሠራም ነው ሰዎች እሱ ላይ ያተኮሩት” ሲል ሮይ ስሚዝ ያብራራል።
ከየካቲት እስከ ግንቦት፤ ቢል ጌትስን ከኮሮናቫይረስ ጋር የሚያገናኙ ሐሰተኛ ትንተናዎች 1.2 ሚሊዮን ጊዜ በቴሌቭዥን ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ መሰራጨታቸውን የኒው ዮርክ ታይምስ እና ዚንጋል ላብስ ጥናት ያሳያል።
በፌስቡክ የቡድን ገፆች የተጋሩ መልዕክቶች ለሚሊዮኖች ደርሰዋል። መረጃዎቹ አሁን ደሞ በቲክቶክ ላይ በስፋት እየተሰራጩ ይገኛሉ።
የቢቢሲ እውነታ አጣሪ ቡድን ከተናፈሱት ወሬዎች መካከል ጥቂቱን አጣርቷል። እነዚህም. . .
- ቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በአፍሪካ እና በሕንድ ህፃናት ላይ ክትባት ሞክረዋል። በዚህም ብዙ ሺዎች ሞተዋል፤ የአካል ጉዳት ደረሰባቸውም አሉ። አንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ጽሑፍ ቢል ጌትስ በሕንድ ተከሰዋል እስከማለት ደርሷል።
- በኬንያ የጽንስ የሚያቋርጥ እንክብልን ጨምሮ የቲታነስ ክትባት እያሰራጩ ነው።
- ‘ዘ ኒው አሜሪካን’ በተባለ መጽሔት የፌስቡክ ገፅ ላይ፤ በክትባት እና ጽንስ በሚያቋርጥ እንክብል የዓለም ሕዝብ ቁጥርን ለመቀነስ ወጥነዋል ተብሎ ተጽፏል። ቢል ጌትስ ከቻይና የኮምኒስት ፓርቲ ጋር ትስስር አላቸው የሚለው ጽሑፍ 6,500 ጊዜ ተጋርቶ 200,000 ጊዜ ታይቷል።
- ማይክሮቺፕ በሰዎች አካል ላይ ሊቀብሩ ነው የሚለው ቪድዮ ዩቲውብ ላይ ሁለት ሚሊዮን ጊዜ ታይቷል።
ሀብታምና ዝነኛ
የማይክሮሶፍት መስራች ነው። ከባለቤቱ ሜሊንዳ ጌትስ ጋር በጥምረት የሚመሩት የተራድኦ ድርጅት ለሕብረተሰብ ጤና በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ሰጥቷል። ታድያ ይህ ቢሊየነር እንዴት የሴራ ትንተና ማጠንጠኛ ሆነ?
በዩኒቨርስቲ ኦፍ ማያሚ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር ጆሴፍ ኡሲንስኪ ስለ ሴራ ትንተናዎች መጻሕፍት ጽፈዋል። ቢል ጌትስ ለሴራ ትንተና የተጋለጡት ሀብታምና ዝነኛ ስለሆኑ ነው ብለው ያምናሉ
"የሴራ ትንተና ኃያላን ሰዎች ክፉ ነገር አድርገዋል ብሎ መክሰስ ነው። ትንታኔዎቹ አይቀያየሩም። ኢላማ የሚያደርጓቸው ሰዎች ግን ይለዋወጣሉ” ሲሉ ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ።
ከቢል ጌትስ በፊት ጆርጅ ሶሮስ፣ የኮች ወንድማማቾች፣ የሮትቻይልድስ ቤተሰቦችና የሮከፌለር ቤተሰቦችም የሴራ ትንተና ኢላማ እንደነበሩ ያጣቅሳሉ።
"ብዙ የሴራ ትንተናዎች ይከስማሉ። ዘለግ ላለ ጊዜ የሚቆዩት ሰዎች ግድ የሚሰጣቸውን ነገር በማንሳት ኃያላን ላይ ያነጣጠሩት ናቸው።”
ሰዎች ማይክሮቺፕ አካላችን ውስጥ ሊቀበር ነው ብለው ስለሚፈሩ ሀብታም ሰዎችና ግዙፍ ተቋሞች፤ ‘ቺፕ ሊቀብሩባችሁ ነው’ ይባላል የሚሉት ምሁሩ “ለዘመናት የሴራ ትንተና ግብ ይህ ነበር። ምንም እንኳን እውነት ባይሆኑም ሰዎች ያምኗቸዋል” ሲሉ ይተነትናሉ።
ያሁ ኒውስ እና ዩ ገቭ በሠሩት የዳሰሳ ጥናት መሠረት፤ ከአንድ አራተኛ በላይ አሜሪካውያን እና 40 በመቶ የሚሆኑ ሪፐብሊካኖች ቢል ጌትስ በኮቪድ-19 ክትባት ሰበብ ማይክሮቺፕ የመቅበር አጀንዳ አላቸው ብለው ያምናሉ።
ሮይ ስሚዝ እንደሚለው ከሆነ፤ “ብዙ ጊዜ ትንሽ እውነት ይያዝና መረጃው ከአውድ ይወጣል።”
ለምሳሌ የቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ተቋም አምና ለአሜምአይቲ የገንዘብ ድጋፍ አድርጎ ነበር። ህሙማን የወሰዷቸውን የክትባት አይነቶች ለሰው ልጅ በግልጽ በማይታይ ሁኔታ ከቆዳቸው በታች ማስቀመጥ ላይ ላተኮረ ጥናት ነበር ድጎማ የሰጡት።
የሴራ ትንተናዎችን መነሻ ማወቅ አዳጋች ነው። ኢንተርኔት ግን በስፋት እንዲሰራጩ መንገዱን ጠርጎላቸዋል።
በተለይም በዚህ ወቅት በወረርሽኙ ሳቢያ የበርካቶች ሥነ ልቦና ስስ መሆኑን ሮይ ይጠቅሳል። ይህም ለሴራ ትንተና ጆሮ እንዲሰጡ ማድረጉ አልቀረም።
“የቀውሱ መጠን ከሚገመተው በላይ እየሆነ ነው። በየጊዜው አዳዲስ ጥናቶች ሲወጡ ለሰዎች የሚሰጠው ምክርም እየተለዋወጠ ነው። ስለዚህም በርካቶች ተጠራጣሪ ሆነዋል።”
እንዲህ ያለ ውዝግብ ሲፈጠር፤ ሰዎች በማኅበረሰብ ደረጃ ትርጉም ይሰጣል ያሉትን መረጃ ወደመቀበል ያዘነብላሉ።
“ለጥያቄዎቻችን መልስ ለማግኘት ያገኘነውን መረጃ ሁሉ እንሰበስባለን። ከመረጃዎቹ መካከል የሴራ ትንተናም ይገኝበታል። ያለውን የመረጃ ክፍተት እየሞሉ ያሉት ቢል ጌትስን የተመለከቱ የሴራ ትንተናዎች ናቸው።”
“ከቺፕ [ማይክሮቺፕ] ጋር የሚያገኛኘው ነገር የለም”
ቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ተቋም ኮሮናቫይረስን ለመዋጋት 330 ሚሊዮን ዶላር መድበዋል። እየተሰራጨ ያለውን ሐሰተኛ መረጃም ፈገግ ብለው ማሳለፍ መርጠዋል።
ለቢቢሲ በላኩት መግለጫ፤ “የሴራ ትንተናዎቹ በበይነ መረብ ተሰራጭተው የማኅበረሰቡ ጤና ላይ ተጽእኖ ያሳድራሉ ብለን እንሰጋለን” ብለዋል። አክለውም. . .
"ዓለም ያልተጠበቀ የጤና እና የምጣኔ ሀብት ቀውስ ውስጥ ባለችበት ወቅት ሰዎች ሐሰተኛ ወሬ ማናፈሳቸው ያስጨንቃል። ሁላችንም የሰዎችን ሕይወት ለመታደግ መተባበር ነው ያለብን። የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት እውነተኛ መረጃ ብቻ ማስተላለፍ ያሻል።”
ቢል ጌትስ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የሴራ ትንተና መነሻ በመሆናቸው መደነቃቸውን እንዲህ ገልጸዋል።
"ክትባቱ ሲገኝ 80 በመቶ የማኅበረሰቡ አካል እንዲወስደው እንፈልጋለን። ከጀርባው ሴራ አለ ብለው ክትባቱን ካልወሰዱ በሽታው ሰዎችን መግደሉን ይቀጥላል። ትኩረቱ እኔ ላይ መሆኑ አስደንቆናል። እኛ ገንዘብ ብቻ ነው የሰጠነው። ሕፃናትን ከበሽታው መከላከል እንፈልጋለን። ከቺፕ [ማይክሮቺፕ] ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። አንዳንዴ እኮ የሚባለው ነገር አስቂኝ ነው።”












