ማይክሮሶፍት ጋዜጠኞችን በሮቦቶች ሊተካ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማይክሮሶፍት በኤምኤስኤን ድረ ገጹ ላይ ይሠሩ የነበሩ በርካታ ጋዜጠኞችን፤ ዜና በሚያስሱ ‘ሮቦቶች’ ሊተካ መሆኑን የአሜሪካና የዩናይትድ ኪንግደም መገናኛ ብዙኃን አስታወቁ።
አሁን ለኤምኤስኤን ዜና የሚሰበስቡት፣ ርዕስ የሚሰጡት፣ ፎቶ የሚያስገቡትም ጋዜጠኞች ናቸው።
ሳተላይት ኒውስ እንደዘገበው ከሆነ ግን ከዚህ በኋላ ይህ ሥራ በሰው ሠራሹ ‘አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ’ ይተካል። ማይክሮሶፍት ውሳኔው ንግዱ ላይ የሚያደርገው ግምገማ አካል መሆኑን ተናግሯል።
“እንደማንኛውም ድርጅት ንግዳችንን በየጊዜው እንገመግማለን። ይህ በአንዳንድ አካባቢዎች ኢንቨስትመንት እንዲጨምር ያግዛል። በአንዳንድ ቦታዎች የነበሩ ተቀጣሪዎች ወደሌላ ቦታ ሊዘዋወሩም ይችላሉ። ውሳኔው ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር አይገናኝም” ሲል ማይክሮሶፍት መግለጫ አውጥቷል።
ማይክሮሶፍት እንደሌሎች የቴክኖሎጂ ተቋሞች ሁላ ለመገናኛ ብዙኃን ገንዘብ በመክፈል ዘገባቸውን በድረ ገጹ ላይ ያትማል። የቀጠራቸው ጋዜጠኞች የትኛው ዘገባ በድረ ገጹ መውጣት እንዳለበት ይወስኑ ነበር።
አዲሱን የማይክሮሶፍት ውሳኔ ተከትሎ፤ 50 የአጭር ጊዜ ቅጥረኛ ጋዜጠኞች ሰኔ መጨረሻ ላይ ከሥራ ይሰናበታሉ ሲል ሲያትል ታይምስ ዘግቧል። የሙሉ ጊዜ ተቀጣሪ ጋዜጠኞች ግን በሥራቸው ላይ ይቆያሉ።
ከሥራ ከሚሰናበቱት አንዱ “ማሽኖች እኛን ተክተው ሥራችንን እንደሚሠሩ ማሰብ ሞራል ይነካል” ብለዋል ለሲያትል ታይምስ።
ሥራቸውን በ ‘አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ’ ከተነጠቁ ጋዜጠኞች አንዳንዶቹ፤ ማሽን የሙያውን መርህ ተከትሎ ዘገባ መምረጥ ስለማይችል፤ አንዳንድ ተገቢ ያልሆኑ ዜናዎች በማይክሮሶፍት ገጽ ላይ ሊወጡ ይችላሉ ብለዋል።
ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፤ ከሥራ ከሚሰናበቱት ጋዜጠኞች 27ቱ የዩኬው ፒኤ ተቀጣሪዎች ናቸው።
“አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ እንዴት የሁላችንንም ሥራ እንደሚቀማን ብዙ አንብቤያለሁ። ይኸው አሁን የኔንም ሥራ ቀማኝ” ሲሉ ተናግረዋል።
ማይክሮሶፍት ወጪ ለመቆጠብ ማሽንን የተመረኮዘ የሚዲያ ሥራ (ሮቦት ጆርናሊዝም) ላይ ምርምር ከሚያደርጉ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋሞች አንዱ ነው።
ጉግልም በመሰል ፕሮጀክቶች ላይ ገንዘቡን ያፈሳል።












