ትራምፕ የአሜሪካና የዓለም ጤና ድርጅትን ግንኙነት አቋረጡ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ያላትን ግንኙነት እያቋረጡ መሆኑን አስታወቁ።

ድርጅቱ ቻይናን ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተጠያቂ ማድረግ ሳይችል ቀርቷል ሲሉ ወንጅለዋል።

ቻይን ለመቅጣት የሚወስዷቸውን እርምጃዎች ይፋ ሲያደርጉ “ቻይና የዓለም ጤና ድርጅትን ሙሉ በመሉ ትቆጣጠረዋለች” ብለዋል።

አገራቸው ለድርጅቱ ታደርግ የነበረውን ድጋፍ ወደሌሎች አካላት እንደምታዘዋውርም ተናግረዋል።

አሜሪካ ለዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርጉ አገሮች ግንባር ቀደሟ ናት። ባለፈው ዓመት ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ደጉማለች።

ዳግመኛ ለመመረጥ ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉት ትራምፕ በአሜሪካ የወረርሽኙን ሥርጭት ለመቆጣጠር ተገቢውን እርምጃ አልወሰዱም ተብለው ይተቻሉ። እሳቸው ደግሞ ቻይና በሽታውን ለመደበቅ ሞክራለች ሲሉ ይከሳሉ።

በአሜሪካ ከ 102,000 በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ቁጥሩ ከመላው ዓለም ከፍተኛው ነው።

ትራምፕ ያሉት ምንድን ነው?

በዋይት ሃውስ በሰጡት መግለጫ “ዛሬ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ያለንን ግንኙነት እናቋርጣለን። እናደርግ የነበረውን ድጋፍ ወደሌሎች ዓለም አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና በጎ አድራጊዎች እናዘዋውራለን” ብለዋል።

በቻይና መንግሥት ስህተት ዓለም እየተሰቃየ ነው ሲሉም ፕሬዘዳንቱ ተደምጠዋል።

“ቻይና የ100 ሺህ አሜሪካውያንን ሕይወት የቀጠፈ ወረርሽኝ ቀስቅሳለች” ያሉት ትራምፕ፤ የዓለም ጤና ድርጅት “ዓለምን እንዲያሳስት” ቻይና ጫና እንዳሳደረችም ተናግረዋል።

ትራምፕ ከባለፈው ወር ጀምሮ የዓለም ጤና ድርጅትን ሲወቅሱ ነበር። ድርጅቱ “መሠረታዊ ኃላፊነቱን” አልተወጣም ብለው፤ የአሜሪካን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያቋርጡ ሲዝቱም ነበር።

ለድርጅቱ ዋና ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም በጻፉት ደብዳቤ “የእርስዎና የድርጅቶ የተሳሳቱ ውሳኔዎች ዓለምን በእጅጉ ዋጋ እያስፈሉ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

ድርጅቱን “የቻይና አሻንጉሊት” ሲሉ ሰይመዋል።

ቻይና በሽታው በአሜሪካ ውስጥ ስለመሰራጨቱ ተጠያቂ የምትሆነው አሜሪካ ራሷ ናት ብላለች። በሽታው የተሰራጨው “በሚዋሹ ፖለቲከኞች” ምክንያት ነውም ብላለች።

በዚህ ወር መባቻ ላይ የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ዛሆ ሊጃን፤ ዶናልድ ትራምፕ ሕዝቡን ለማሳሳት እየሞከሩ ነው ብለው ነበር። “ቻይናን በመኮነን የአሜሪካን ደካማ ምላሽ ለመሸፋፈን እየሞከሩ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት አባል አገራት በበኩላቸው ለወረርሽኙ የተሰጠውን ዓለም አቀፋዊ ምላሽ የሚያጣራ ገለልተኛ ቡድን ለማዋቀር ተስማምተዋል።