ለጥቁር አሜሪካዊው ግድያ ፍትህ የሚጠይቁ አሜሪካውያን ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸው ቀጥሏል

ግጭት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በሚኒያፖሊስ ከተማ ያልታጠቀው ጥቁር አሜሪካዊ በነጭ ፖሊስ ከተገደለ በኋላ ለግድያው ፍትህ የሚጠይቁ አሜሪካያን በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸውን ቀጥለዋል።

የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ለመቃውም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ትናንት ምሽት ዋይት ሃውስ ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ አድርገው የነበረ ሲሆን፤ ባለስልጣናት አከባቢውን ከእንቅስቃሴ ውጪ በማድረግ ዘግተውታል።

ሚኒሶታ፣ ኒው ዮርክ፣ አትላንታ፣ ቴክሳስ እና ሌሎች ግዛቶችም አመጽ የተሞላበት የተቃውሞ ሰልፎችን አስተናግደዋል። ለጆርጅ ፍሎይድ ሞት ተጠያቂ ነው የተባለው የቀድሞ የሚኒያፖሊስ ከተማ የፖሊስ ባልደረባ ያግድያ ክስ ተመስርቶበታል።

ዴሪክ ቹቪየን የተባለው የቀድሞ የፖሊስ ባልደረባ የ46 ዓመቱን ያልታጠቀ ጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድን እጁን ወደ ኋላ አስሮ አንገቱን በጉልበቱ አፍኖ ከመሬት አጣብቆ ይዞት የሚያሳያው ምስል በርካቶች ተጋርተውታል። ጆርጅ ፍሎይድ በወቅቱ "መተንፈስ አልቻልኩም፤ እባክህ አትግደለኝ" ሲል ነጭ አሜሪካዊውን እየተማጸነ ነበር።

ዴሪክ ቹቪያን የተባለው 44 ዓመት ፖሊስ የፊታችን ሰኞ ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሏል።

ሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ አርብ አመሻሽ ላይ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ አርብ አመሻሽ ላይ።

ሚኒሶታ ከየትኛውም ግዛት በበለጠ ከፍተኛ ተቃውሞ ያስተናገደች ግዛት ናት። በሚኒያፖሊስ-ሴንት ፖል ሰዓት እላፊ ማወጅም ግድ ብሏል። ሰልፈኞች ግን የሰዓት እላፊ አዋጁን ወደ ጎን በመተው ፖሊስ ጣቢያዎችን እና የፖሊስ ተሽከርካሪዎችን በእሳት ሲያጋዩ ታይተዋል።

ግርግሩን በመጠቀም ዘረፋ የሚፈጽሙም ታይተዋል። የከተማዋ ፖሊስ የተቀሰቀሱ አመጾችን መቆጣጠር ተስኖት ተስተውሏል። ለዚህም ይመስላል ፔንታጎን በሚኒያፖሊስ የአገሪቱ ጦር ሊሰማራ እንደሚችል ፍንጭ የሰጠው።

በአትላንታ ህዝብ እና ንብረት ለመጠበቅ በሚል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል። የተቃውሞ ድምጻቸውን ለማሰማት በሲኤንኤን ደጃፍ በርካቶች ከተሰባሰቡ በኋላ፤ ህንጻዎችን ተዘርፈዋል፤ የፖሊስ መኪኖችም በእሳት ጋይተዋል።

አትላንታ ጆርጂያ ሲኤንኤን ቢሮ አቅራቢያ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አትላንታ ጆርጂያ ሲኤንኤን ቢሮ አቅራቢያ

በኒው ዮርክ ግዛት ብሩክሊን አከባቢም በተመሳሳይ ሁኔታ የተቃውሞ ሰልፉ ወደ አመጽ ተቀይሮ ሰልፈኞች የፖሊስ ተሽከርካሪዎችን አውድመዋል። በርካታ የፖሊስ ባልደረቦችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ቁጥራቸው በውል ያልታቁ ሰዎችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ከንቲባ ቢል ዲ ብላሲኦ "እንዲህ አይነት ምሽት ዳግም ማየት አንሻም" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ለይ አስፍረዋል።

በዳላስ ቴክሳስ፤ ፖሊሶች ተቃዋሚዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተኩሰዋል። በሎስ አንጀለስ ደግሞ ተቃዋሚዎች ዋና መንገዶችን ዝግ አድርገዋል።