በአሜሪካ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ፖሊስ ጣቢያ አቃጠሉ

በእሳት የቃተለው ፖሊስ ጣቢያ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በእሳት የቃተለው ፖሊስ ጣቢያ
ታትሟል

በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለ ጆርጅ ፍሎይድ ሕይወቱ ካለፈች በኋላ ለሦስተኛ ቀን በቀጠለ ተቃውሞ ሰልፈኞች ሚኒያፖሊስ ውስጥ የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በእሳት አጋይተዋል።

ፍሎይድ ምንም እንኳን ‘’መተንፈስ አልቻልኩም ‘’ እያለ በተደጋጋሚ ቢጮህም ይዞት የነበረው ፖሊስ በጉልበቱ አንገቱን ተጭኖት ለረዥም ጊዜ ቆይቷል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ‘ወሮበላዎች’ የፍሎይድን ክብር በመጥፎ ተግባራቸው እያቆሸሹት ነው በማለት የአገሪቱ ብሔራዊ ዘብ በአካባቢው ጸጥታ እንዲያስከብር አዘዋል።

የፍሎይድ ቤተሰቦች ለሞት ምክንያት ናቸው የተባሉት አራት የፖሊስ አባላት በግድያ ወንጀል እንዲከሰሱ ቢጠይቁም አቃቤ ሕግ ግን ገና መረጃዎችን እየሰበሰብኩ ነው ብሏል።

የተቃውሞ ሰልፉን ሲዘግብ የነበረው የሲኤንኤን ጋዜጠኛ ኦማር ሂሜኔዝና የካሜራ ባለሙያው ደግሞ የቀጥታ ዘገባ ላይ እያሉ በሚኒሶታ ስቴት ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ፖሊስ በወቅቱ ጋዜጠኞቹ ከአካባቢው ዞር ባለማለታቸው ነው በቁጥጥር ስር ያዋልኳቸው ብሏል። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ደግሞ የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ይቅርታ ከጠየቁ በኋላ ተለቀዋል።

በተጨማሪም እንደ ኒው ዮርክ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ቺካጎ፣ ዴንቨር፣ ፊኒክስ እና ሜምፊስ በመሳሰሉ የተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል።

ሐሙስ ዕለት ሰልፈኞች ፍሎይድን በቁጥጥር ስር ያዋሉት የፖሊስ አባላት የሚገኙበት የፖሊስ ጣቢያ አካባቢ ተሰባስበው ነበር።

የፖሊስ አባላትም አስለቃሽ ጭስና የፕላስተክ ጥይቶችን በመጠቀም ሰልፈኞቹን ለመበተን ሲሞክሩ ነበር።

ሰኞ ልብ የሚነካው የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ በማኅበራዊ ገጾች ከተሰራጨ በኋላ ከማክሰኞ ጀምሮ የተቃውሞው መጠን እየጨመረ መጥቷል።

የሚኒያፖሊስ ከንቲባ ጃኮብ ፍሬይ የፍሎይድ ሞት እንዳሳዘናቸው ገልጸው በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት ፖሊስ ጣቢያውን ወደሌላ ቦታ ለማዘዋወር መገደዳቸውን አስታውቀዋል።

ከጆርጅ ፍሎይድ ሞት ጋር ተያይዞ አንገቱ ላይ በጉልበቱ የቆመበትን ነጭ ፖሊስ ጨምሮ ሌሎች ሦስት ተባባሪ ፖሊሶች ለጊዜ ከሥራቸው እንዲታፈዱ ብቻ ተደርጓል።

በሜኒያፖሊስ ተቃውሞው ከቁጥጥር ውጪ በመውጣቱ በከተማው ከንቲባ ጥያቄ መሰረት የሜኔሶታ ክፍለ ግዛት ገዢ ቲም ዋልትዝ ብሔራዊ ዘብ ወደ ስፍራው እንዲንቀሳቀስ ፈቅዷል።

"የጆርጅ ፍሎይድ ሞት ወደ ውንብድናና ዝርፊያ ሊወስደን አይገባም። የፍትህ ሥርዓት እና አሠራር ለውጥን ነው መጠየቅ የሚኖርብን" ሲሉም ለከተማዋ ነዋሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።