ኮሮናቫይረስ፡ ቤተ-ክርስቲያኗ ርቀትን በመጠበቅ መስገድ ላልቻሉ ሙስሊሞች በሯን ክፍት አደረገች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ በአንድ መስጅድ ለመስገድ ለተጣበቡ ሙስሊሞች በበርሊን የምትገኝ አንዲት ቤተ-ክርስቲያ በሯን ከፈተችላቸው።
ጀርመን ከሦስት ሳምንት በፊት የ1.5 ሜትር አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ሐይማኖታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ፍቃድ ሰጥታ ነበር።
ይሁን እንጂ በበርሊን የሚገኘው ዳር አሳላም መስጅድ የእምነቱ ተከታዮች የሚፈለገውን ያህል ርቀት በመጠበቅ ሐይማኖታዊ ሥርዓቱን ለማካሄድ የነበራቸው ቦታ በቂ አልነበረም።
ይሁን እንጂ በከተማው የሚምትገኘው ማርታ ሉተርን ቤተ-ክርስቲያን የጁምዓ ጸሎት በቤተ-ክርስቲያኗ ውስጥ እንዲደረግ ፍቃድ ሰጥታለች።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
"ይህ አስደሳች ነው። በዚህ ረመዳን ወር እና ወረርሽኝ ወቅት ይህ ምልክት ሐሴትን ይፈጥራል" ሲሉ የመስጅዱ ኢማም ለሬውተርስ ዜና ወኪል ተናግረዋል። "ይህ ወረርሽኘ አንድ ማኅብረሰብ አድርጎናል። ችግር ሰዎችን አንድ ላይ ያመጣል" ብለዋል ኢማሙ።
በቤተ-ክርስቲያኗ ውስጥ ከሌሎች ሙስሊሞች ጋር ጸሎቱን ያደረገው ሳሚር ሃምዱን፤ "የሙዚቃ መሳሪያዎቹን እና ስዕሎቹን ስመለከተ ግራ የሚያጋባ ስሜት ፈጥሮብኛል። ነገር ግን ዝርዝር ነገሮችን ካልተመለከትን በቀር ይህም እኮ የፈጣሪ ቤተ-ነው" ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቤተ-ክርስቲያኗ አገልጋይ ጭምር በቤተ-ክርስቲያኗ ውስጥ በተደረገው የጁምዓ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ተካፋይ ነበሩ።
"በጀመርንኛ ቋንቋ ንግግር አድርጊያለሁ" ይላሉ ሞኒካ ማቲያስ። "በጸሎቱ ወቅት አዎ፣ አዎ፣ አዎ ብቻ ነበር ማለት የቻልኩ። አንዱ ስለሌላው የነበረው ሁኔታ አስደሳች ስሜትን የሚፈጥር ነበረ" ብለዋል የቤተክርስቲያኗ ፓስተር።














