ሃንጋሪ ፆታ መቀየርን ከለከለች

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአውሮፓዊቷ አገር ሃንጋሪ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ከተወለዱ በኋላ ፆታ መቀየር አይቻልም ሲል ደነገገ።
ከተወደሉ በኋላ ፆታቸውን በቀዶ ጥገና የሚቀይሩ ሰዎች በትውልድ ሠርተፊኬታቸው ላይ ከተመዘገበው የተለየ ፆታ ሊኖራቸው አይችልም ሲል ነው ምክር ቤቱ የደነገገው።
ፊደስ የተሰኘው ቀኝ ዘመሙ ገዥ ፓርቲ ያረቀቀው ይህ ሕግ በ133 የድጋፍ ድምፅና በ57 ተቃውሞ ፅድቋል።
የመብት ተሟጋች ቡድኖች ሕጉ በእንግሊዝኛው ምሕፃረ-ቃል ኤልጂቢቲኪው የተሰኙትን ዜጎች መብት የበለጠ ይጋፋል ሲል ይሞግታሉ። አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ሕጉን 'ሰይጣናዊ' ሲሉ ጠርተውታል።
ፆታቸውን የሚቀይሩ ሰዎችና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች፤ ወግ አጥባቂው የሃንጋሪ መንግሥት ራሳቸውን በነፃነት መግለፅ የሚፈልጉ ሰዎች ላይ የከፈተው ጦርነት ነው ሲሉ አዲሱን ሕግ አጥብቀው ይቃወማሉ።
'ለበርካታ ጊዜያት ራስን ማጥፋት የሚለው ሐሳብ በአእምሯቸው ብቅ ብሎ የማያውቅ ሰዎች አሁን ግን ተስፋ ቆርጠዋል። ድንጋጤ ውስጥ ናቸው። ሰዎች ሃንጋሪን ጥለው ሌሎች ፆታቸውን ወደ ሚቀበሉ ሃገራት መፈርጠጥ ጀምረዋል' ይላሉ አንድ የመብት ተሟጋች።
ነገር ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን የተመራው ገዥው ፓርቲ አዲሱ ድንጋጌ ሕጋዊ አለመግባባቶችን ያስወግዳል ሲል ይከራከራል።
ከዚህ በፊት ፆታቸውን የቀየሩ ሰዎች የልደት ማስረጃቸውን ለመንግሥት ባለሥልጣናት ማሳየት እየተሳቀቁ እንደሆነ ተነግሯል።
አዲሱ ረቂቅ ሕግ ወደ ፕሬዝደንት ጃኖስ አደር ያመራል። ፕሬዝደንቱ ደግሞ የገዠው ፊደስ ፓርቲ አባል ናቸው። ሕጉ ተግባራዊ እንዲሆን ፕሬዝደንቱ ፊርማቸውን ሊያኖሩበት ይገባል። የመብት ተሟጋቾች ግን ፕሬዝደንቱ እንዳይፈርሙበት ግፊት እያደረጉ ነው።
በርካታ የአውሮፓ ሃገራት ሰዎች ፆታውን ሲቀይሩ የልደት ማስረጃቸው ላይም እንዲቀየር ይፈቅዳሉ።












