"ኮሮናቫይረስን ማጥፋት ባይቻል መቆጣጠር ይቻላል" ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኮሮናቫይረስ "ፈጽሞ ላይጠፋ ይችላል" ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ።
ይህንን የተናገሩት የድርጅቱ የአስቸኳይ ጊዜ ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ማይክ ሪያን፤ ቫይረሱ መቼ ሊወገድ ይችላል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በመለሱበት ወቅት ነው።
ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም እንዳሉት በሽታውን ማጥፋት ባይቻል ጥረት ከተደረገ መቆጣጠር እንደሚቻል አመልክተዋል።
ጨምረውም ለበሽታው ክትባት ቢገኝ እንኳን፤ ቫይረሱን ለመቆጣጠር "ግዙፍ ጥረት" ማድረግን ይጠይቃል ብለዋል።
"ይህ ቫይረስ ፈጽሞ ላይጠፋና ከሰው ልጅ ጋር አሁን ድረስ እንደቆዩት በሽታዎች አንዱ ሆኖ በኅብረተሰቡ ውስጥ ሊኖር ይችላል" ሲሉ ነው ዶክተር ሪያን ጄኔቫ ላይ በተደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተናገሩት።
አክለውም "ኤችአይቪ አልጠፋም፤ ነገር ግን ቫይረሱን በተመለከተ መደረግ ያለበትን እያደረግን ነው" ሲሉ ምሳሌ ጠቅሰዋል።
ዶክተሩ "የኮሮናቫይረስ መቼ ሊወገድ እንደሚችል ማንም ሰው ሊተነብይ አይችልም" ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ ከ100 በላይ ለኮሮናቫይረስ ይሆናሉ የተባሉ ክትባቶች ላይ ምርምር እየተደረገ ቢሆንም፤ ዶክተር ሪያን እንዳሉት ክትባት በሽታውን ላያጠፋው ይችላል።
እንደ ምሳሌም ኩፍኝን አንስተው ምንም እንኳን የመከላከያ ክትባት ቢኖረውም እስካሁን ድረስ ሊጠፋ እንዳልቻለ ተናግረዋል።
ሌላኛዋ የድርጅቱ ኃላፊ ማሪያ ቫን ኬርኮቫ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ "ከዚህ ወረርሽኝ ለመውጣት የተወሰነ ጊዜ እንደሚወስድብን ማሰብ ይኖርብናል" ብለዋል።
እስካሁን በዓለም ዙሪያ ወደ 300 ሺህ የሚጠጋ ሰው በኮቪድ-19 ምክንያት የሞተ ሲሆን ከ4.3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ በበሽታው መያዛቸው ይታወቃል።














