የኢራን ባሕር ኃይል በስህተት በተኮሰው ሚሳኤል 19 ባህረተኞች ሞቱ

ሆርሙዝ ሰርጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አደጋው አጋጠመበት የተባለው የሆርሙዝ ሰርጥ
ታትሟል

አንድ የኢራን ባሕር ኃይል መርከብ በስህተት በራሱ ወገን መርከብ ላይ በተኮሰው ሚሳኤል አስራ ዘጠኝ በሕረተኞች ሲሞቱ ሌሎች 15 ደግሞ መቁሰላቸውን የአገሪቱ ባሕር ኃይል አስታወቀ።

የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙሃን እንዳሉት እሁድ ዕለት በኦማን ባሕረ ሰላጤ ላይ ጃማራት የተባለችው ፈጣን የጦር መርከብ አዲስ የተገጠመላትን ጸረ መርከብ ሚሳኤል በምትሞክርብት ጊዜ ነው ኮናራክ የተባለችውን ቀላል የባሕር ኃይሉን መርከብ መትታ ጉዳቱ የደረሰው።

አደጋው ያጋጠመው ባሕር ኃይሉ በሆርሙዝ ሰርጥ አቅራቢያ ወታደራዊ ልምምድ እያደረገ በነበረበት ጊዜ እንደሆነም ተገልጿል።

የኢራን ጦር ኃይሎች ወሳኝ ጠቀሜታ ባለው በዚህ የባሕር ላይ መተላላፊያ በመደበኛነት የጦር ልምምድ እንደሚያደርጉ ተነግሯል።

"ኮናራክ መርከብ ትናናት [ዕሁድ] ከሰዓት በኋላ ባንዳር-ኢ ጃስክ በተባለው አካባቢ እየተደረገ በነበረው ወታደራዊ ልምምድ ወቅት በሚሳኤል ተመትታላች" ሲል የአገሪቱ መንግሥት ቴሌቪዥን በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል። ቦታው በደቡባ ዊ ኢራን ካለው የባሕር ዳርቻ ወጣ ብሎ የሚገኝ ነው።

"መርከቧ በሚሳኤል ልትመታ የቻለችው ለልምምድ ኢላማነት የተቀመጠው ቁስ ወደ መርከቧ አቅራቢያ በመጠጋቱና በመካከላቸው በቂ እርቀት ስላልነበረ የተፈጠረ ነው" ሲል ጣቢያው ጨምሯለው።

ይህ በስህተት የተፈጠረው አደጋ ያጋጠመው ከኢራኗ ዋና ከተማ ቴህራን 1,270 ኪሎ ሜትሮች ርቃ ከምትገኘው ጃስክ ከተባለችው ወደብ አቅራቢያ የኦማን ባሕረ ሰላጤ ውስጥ መሆኑም ተገልጿል።

ጃማራን እና ኮናራክ የተባሉት የጦር መርከቦች በኢራን ጦር ሠራዊት ውስጥ የአገሪቱ ባሕር ኃይል ንብረቶች ናቸው።

በማኅበራዊ የመገናኛ መድረኮች ላይ አደጋውን በተመለከተ የሚዘዋወሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ባሕረተኞች ወደ አንቡላንስ ሲጓጓዙ ያሳያሉ።

ከአራት ወራት በፊት ኢራን ከአሜሪካ ጋር ከባድ ፍጥጫ ውስጥ በነበረችበት ወቅት የኢራን አብዮታዊ ዘብ የዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላንን ዋና ከተማዋ ቴህራን አቅራቢያ በስህተት መትቶ በመጣሉ የ176 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።