ኮሮናቫይረስ በአፍሪካ እስከ 190 ሺ ሰዎችን በመጀመሪያው ዓመት ሊገድል ይችላል- የዓለም ጤና ድርጅት

ሴኔጋል

የፎቶው ባለመብት, JOHN WESSELS

ታትሟል

ኮሮናቫይረስ በአፍሪካ እስከ 190 ሺ ሰዎችን በመጀመሪያው ዓመት ሊገድል ይችላል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ።

የዓለም ጤና ድርጅት ትናንት ማምሻውን በሰጠው መግለጫ ኮሮናቫይረስ በመጀመሪያው ዓመት ብቻ በአፍሪካ ከ 83 ሺ እስከ 190 ሺ ሰዎችን ሊገድል እንደሚችል አስታውቋል።

በተጨማሪም ቫይረሱ በቶሎ በቁጥጥር ስር የማይውል ከሆነ ከ29 ሚሊየን እስከ 44 ሚሊየን ሰዎች በቫይረሱ ሊጠቁ ይችላሉ ብሏል ድርጅቱ።

‘’የዓለም ጤና ድርጅት ይህንን ግምት የሰራው አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት ቫይረሱን ባለበት ለማስቆም እየወሰዱት ያለው እርምጃ በቂ አለመሆን ብቻ ሳይሆን ከሚገባው በታች በመሆኑ ነው’’ ብለዋል የድርጅቱ አፍሪካ ኃላፊ ማትሺዶ ሞዌቲ።

በርካታ አፍሪካ አገራት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ህዝባዊ ስብሰባዎችን ከልክለዋል፤ ዓለማ አቀፍ በረረዎችን አቁመዋል፤ የሰዓት እላፊ ጥለዋል፤ የእንቅስቃሴ ገደብም አበጅተዋል።

ነገር ግን አሁን እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች በቂ አይደሉም፤ ያሉትም ሕጎች በአግባቡ ተግባራዊ እየተደረጉ አይደለም ብሏል የዓለም ጤና ድርጅት።

ቫይረሱ ከሌላው ዓለም ዘግይቶ አፍሪካ በመድረሱ የስርጭቱ መጠን በአሁኑ ወቅት ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ለዓመታት የሚቆይ ወረርሽኝ ሊሆን እንደሚችልም ድርጅቱ ስጋቱን ገልጿል።

‘’ይህ ቫይረስ ለሚቀጥሉት ዓመታት አብሮን ሊቀጥል የሚችልበት እድል ሰፊ ነው። መንግስታት ከአሁኑ ተገቢውን ስራ ካልሰሩ ይህ መሆኑ አይቀርም። በርካታ ሰዎችን መመርመር፣ ንክኪ ያለበትን ቦታ በፍጥነት መለየትና ለታማሚዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ ህክምና መስጠት ወሳኝ ናቸው’’ ብለዋል ማትሺዶ ሞዌቲ።

ድርጅቱ አክሎም እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ አልጄሪያና ካሜሩን ያሉ አገራት በቫይረሱ ክፉኛ ሊጠቁ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።

ይህ የዓለም ጤና ድርጅ የሰራው ጥናት በአህጉሪቱ አባል የሆኑ 47 አገራት ላይ የተሰራ ሲሆን ጂቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ግብጽ፣ ሊቢያ፣ ቱኒዚያና ሞሮኮን አያካትትም።

እስካሁንም በነዚሁ 47 አገራት ከ 35 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከ1200 በላይ ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል ብሏል ድርጅቱ።

አሁን ባለው አካሄድ ከ3.5 ሚሊየን እስከ 5.5 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች ሆስፒታል ሊገቡ እንደሚችሉ የተነበየው ድርጀቱ ከእነዚህ ውስጥ ከ82 ሺ እስከ 167 ሺ የሚሆኑት ከባድ የጤና እክል ያጋጥማቸዋል ብሏል።

በተጨማሪም ከ52ሺ እስከ 107 ሺ የሚደርሱት ደግሞ የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ (ቬንትሌተር) ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጀት አሳስቧል።

ኮሮና