ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኪም ጆንግ ኡን በመታየታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገለፁ

ትራምፕና ኪም ጆንግ ኡን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በመታየታቸውና ጤነኛም መምሰላቸው እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል።

"በመመለሱ ደስተኛ ነኝ፤ እንዲሁም ደህና በመሆኑ" በማለት ትዊተር ገፃቸው ላይ ፕሬዚዳንት ትራምፕ አስፍረዋል።

ለሶስት ሳምንታት የት ሄደው ነው? በሚል አለምን ግራ ያጋቡት ኪም ጆንግ ኡን የማዳበሪያ ፋብሪካ መክፈቻ መመረቂያ ላይ ተገኝተው ነበር።

ከህዝብ እይታ ተሰውረው የነበሩት ኪም ጆንግ ኡን በተለይም በህይወት የሌሉት አያታቸው ልደት ላይ አለመገኘተቻው ለተለያዩ መላ ምቶች በር የከፈተ ሲሆን፤ በጠና እንደታመሙ እንዲሁም በህይወት እንደሌሉም እየተነገረ ነበር።

በዚህ ሳምንት የማዳበሪያ ፋብሪካ ምርቃት ላይ ተገኝተው ሪባን የቆረጡት መሪው በቦታው ላይ ተገኝቶ የነበረው ህዝብም መሪው ብቅ ሲሉ ደስታውን መቆጣጠር አቅቶት፣ በጭብጨባና በሆይታ እንደተቀበሏቸው ኬሲኤንኤ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በወቅቱም በከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም በእህታቸው ኪም ዮ ጆንግ ታጅበው ነበር። በፋብሪካው የአመራረት ብቃት እንደረኩ የተናገሩት መሪው ለአገሪቱም የኬሚካል ኢንዱስትሪም ሆነ የምግብ አቅርቦት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋልም በማለት እንዳሞካሹት የዜና ወኪሉ አክሎ ዘግቧል።

ስለ መሪው የተለያዩ መላምቶችና የሴራ ዜናዎች በሚነገሩበት ወቅት ፕሬዚዳንት ትራምፕም "የት እንዳለ አውቃለሁ ግን መናገር አልችለም። ጤንነት እመኛለሁ" ብለው ነበር።

ፕሬዚዳንት ትራምፕና የሰሜን ኮሪያው መሪ ብዙዎችን ግራ በሚየጋባ ሁኔታ ለየት ያለ ግንኙነትን መመስረት ችለዋል።

ከሁለት አመታት በፊት ሶስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ደብዳቤም ተፃፅፈዋል፤ ትራምፕም "ለየት ያለ ችሎታ ያለው" በማለትም አሞካሽተዋቸዋል።

በመሪው ላይ የሚነገሩ መላምቶች እንዴት ተጀመሩ?

የአዲሲቷ ሰሜን ኮሪያ መስራች የሚባሉት ኪም ኢል ሰንግ የልደት ዝክራቸው በሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠውና ትልቅም ክብረ በአል ነው። በየአመቱም መሪው ኪምም የአያቱን መካነ መቃብር ያረፈበትን ስፍራ ይጎበኛሉ፤ ይህንንም ሳያደርጉ የቀሩበት ጊዜ አልነበረም።

በክብረ በዓሉ ላይ አለመገኘታቸው እንዲሁም አንድ ድረ-ገፅ መሪው እንደታመሙ መዘገቡ ለመላምቶቹ በር ከፈተ።

መሪው በልብ ህመም ይሰቃዩ እንደነበርና በተለይም ባለፈው ነሐሴ ወር ወደ ፓክቱ ተራራ መውጣታቸው ሁኔታውን አባብሶታል ብሏል።

የተለያዩ አለም አቀፍ ሚዲያዎችም አንድ ምንጭ በመጠቀም መዘገብ ጀመሩ።

አንድ የአሜሪካ ሚዲያም ነገሩን ጥግ ወስዶ መሪው የልብ ቀዶ ጥገና ካደረጉ በኋላ በጠና እንደታመሙ ዘገበ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊም ማይክ ፖምፔዮም የሚናፈሱትን ወሬዎች በመንካት የአሜሪካ ባለስልጣናት መሪውን በቅርብ አይተዋቸው እንደማያውቁም ተናገሩ።

ነገር ግን የደቡብ ኮሪያ መንግሥትም ሆነ የቻይና ደህንነት ለሮይተርስ የዜና ወኪል ይህ እውነተኛ ዜና እንዳልሆነ ተናግረው ነበር።

ኪም ጆንግ ኡን ከሕዝብ እይታ ሲርቁ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 2014 አንድ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ከተሳተፉ በኋላ ለአርባ ቀናት ጠፍተው ነበር።

ተመልሰው ሲመጡም ምርኩዝ ይዘው ነበር። የሃገሪቱ ሚዲያም የት እንደነበሩም ምንም አይነት መግለጫም አልሰጠም።

የደቡብ ኮሪያ የደህንነት ኤጀንሲ ግን በግራ እግራቸው ላይ ቀዶ ጥገና አድርገው እንደነበር ገልጿል። መሪው ታመው ነበር? ቀዶ ጥገናስ አድርገዋል? ለሶስት ሳምንታትስ ያህል የት ነበሩ ለሚሉት ጥያቄዎች አሁንም አለም የተለያዩ መላምቶችን ከመሰንዘር ውጭ ምንም ምላሽ ከሰሜን ኮሪያ አልተሰጠም።