ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸው ተሰማ

የተኩስ ልውውጡ የተነሳበት ምክንያት አልታወቀም፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የተኩስ ልውውጡ የተነሳበት ምክንያት አልታወቀም
ታትሟል

ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ ሁለቱን አገራት በምትለያየው የድንበር ከተማ ከጦርነት ነጻ ቀጠና ውስጥ የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸው ተሰማ፡፡

ሰሜን ኮሪያ በፈጸመችው ጥቃት የድንበር ከተማ በሆነችው ቸዎርዎን የሚገኘውን የደቡብ ኮሪያ የጥበቃ ጣቢያ መምታቷን የሴኡል ጦር አስታውቋል፡፡

በደቡብ ኮሪያ በኩል ምንም ዓይነት የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ተገልጿል፡፡

የደቡብ ኮሪያ ጦር በሰጠው መግለጫ "ደቡብ ኮሪያ ለጥቃቱ አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት ሁለት ዙር ተኩስ የፈጸመች ሲሆን በመመሪያው መሠረትም ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች" ብሏል፡፡

መግለጫው አክሎም ባለሥልጣናት ሰሜን ኮሪያን ለማነጋገር ጥረት እያደረጉ እንደነበር አትቷል፡፡

በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሰሜን ኮሪያ ወደ ደቡብ ኮሪያ ስትተኩስ ይህ የመጀመሪያዋ ነው፡፡

በጎርጎሮሳዊያኑ 1953 የኮሪያ ጦርነት በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ጦርነት ለማርገብ ከጦርነት ነጻ ቀጠና ከተማ ተመስርቶ ነበር፡፡

የደቡብ ኮሪኣ መንግሥትም ላለፉት ሁለት ዓመታት በድንበር አካባቢ ያለውን ምሽግ ወደ ሰላማዊ ቀጠና ለመለወጥ ሙከራ አድርጎ ነበር፡፡

ነገር ግን አሁን የተኩስ ልውውጡ የተነሳበት ምክንያት አልታወቀም፡፡

ውጥረቱም የተከሰተው ለሦስት ሳምንታት ከሕዝብ ዕይታ ጠፍተው የነበሩትና ስለጤናቸው ሁኔታ በጎ ያልሆነ ዜና ሲናፈስባቸው የነበሩት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በቴሌቪዥን መስኮት ከታዩ ከአንድ ቀን በኋላ ነው፡፡