ኮሮናቫይረስ፡ የኒው ዮርክ ከተማ በቫይረሱ ክፉኛ ከተጠቁ አገራት ቀዳሚ ሆነች

ታትሟል

በአሜሪካ ካሉ ከተሞች ውስጥ ኒው ዮርክ የቫይረሱ ወረርሽኝ ማዕከል ሆናለች። ከተማዋ በአሜሪካ ብቻ አይደለም በኮሮናቫይረስ ተያዦች ቁጥር ከየትኞቹም አገራት በልጣ ቀዳሚ ሆናለች።

በቅርብ የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው በትናነትናው ዕለት በቫይረሱ የተያዙ ተጨማሪ 10 ሺህ ሰዎች ከመገኘታቸው ጋር ተያይዞ ቁጥሩን 159, 937 አድርሶታል።

ይህም ቁጥር በስፔን ከተያዙት 153 ሺህና በጣልያን 143 ሺህ ሰዎች በላይ ሆኖ ቀዳሚ አድርጓታል።

የቫይረሱ መነሻ በሆነችው ቻይና በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 82 ሺህ ሲሆን 3,300 ሰዎች ሞተዋል።

በአጠቃላይ በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 462 ሺህ ሲሆን 16,500 ሰዎችም ህይወታቸውን አጥተዋል።

በዓለም ላይ ያለውንም አሃዝ በምናይበት ወቅት 1.6 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 95 ሺህ ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

ኒው ዮርክ በቫይረሱ ክፉኛ የተጠቁ አገራትን በቁጥር ብትቀድምም፤ የሟቾችን ቁጥር ስናይ ግን 7 ሺህ ነው የተመዘገበው። በስፔን 15,500 ሰዎች ሞተዋል፤ ከፍተኛ የሟች ቁጥር በተመዘገበባት ጣልያንም የ18 ሺህ ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል።

ከሰሞኑም በኒው ዮርክ ከተማ ከእግር እስከ ራሳቸው ኦከስጅን የተገጠመለት አልባሳት የለበሰሱ ሰራተኞች የጅምላ ቀብር ሥነ ሥርዓት ሲያከናውኑ የሚያሳዩ ፎቶዎች ወጥቷል።

እነዚህ በድሮን የተቀረፁ ምስሎች እንደሚያሳዩት የቀብር ሥነ ሥርዓቱን የሚፈጽሙ ሠራተኞች መሰላል በመጠቀም የሬሳ ሳጥን ተሸክመወው ወደተቆፈረው ትልቅ ጉድጓድ ሲገቡ ነው።

እነዚህ ምስሎች የተወሰዱት ብሮንክስ ከሚገኘው ሃርት አይላንድ ተብሎ የሚጠራው ቦታ ሲሆን፤ ይህ ስፍራም ለ150 ዓመታት ያህል የቀብር ሥነ ሥርዓት ማከናወን ለማይችሉ ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን እንዲቀብሩ የከተማዋ ባለስልጣናት ያዘጋጁት መካነ መቃብር ነው።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኒው ዮርክ ከተማ በሰፊው መዛመትን ተከትሎም በዚህ መካነ መቃብር ላይ የሚቀበሩ ሰዎችም ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርን አሳይቷል።

ከዚህ ቀደም ከራይከርስ አይላንድ የሚመጡ ታራሚዎች ነበሩ ቀብሩን ያከናውኑ የነበሩት፤ በአሁኑ ጊዜ ግን የሟቾች ቁጥሩ በማሻቀቡ ሌሎች ሠራተኞችንም መቅጠር ግድ ሆኗል።

በወረርሽኙ ለሚሞቱ ሰዎች የቀብር ቦታ እጥረት ያጋጥማል በሚልም አንድ የሕዝብ መካነ መቃብር መዘጋጀቱንም የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ቢል ደ ብላሲዮ ገልፀዋል።

በኒው ዮርክ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን በዚህ ሳምንት ረቡዕም 799 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።

ነገር ግን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው ያሉት የከተማ አስተዳዳሪ አንድሪው ኩሞ፤ ለዚህም እንደ ምክንያትነት የሚጠቅሱት በኒው ዮርክ ሆስፒታል ውስጥ የሚገባው ታማሚ ቁጥር በመቀነሱ ነው።

አስተዳዳደሪው እንደተናገሩት አካላዊ ርቀት መጠበቅ በሕዝቡ ዘንድ እየተተገበረ መሆኑ ለዚህ ማሳያ ነው ብለው፤ ቫይረሱን አሜሪካ ካጋጠማት የመስከረም 11ዱ ጥቃት ጋርም ጋር አመሳስለውታል።

በአጠቃላይ በአሜሪካ ያለውን የሟቾች ቁጥር ከተገመተው በታች ሊሆን እንደሚችል የተላላፊ በሽታዎች መቆጣጠሪያ ኃላፊ ዶ/ር አንቶኒዮ ፋውቺ ለኤንቢሲ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከመቶ ሺህ እስከ ሁለት መቶ ሺህ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም ያለውን ሁኔታ በመገምገም እስከ 60 ሺህ ሰዎች ሊሞቱ እንደሚችሉ ዶ/ር አንቶኒዮ ፋውቺ አስረድተዋል።