ሱዳናዊው ፈረንሳይ ውስጥ ሁለት ሰዎችን በስለት ገደለ

ጥቃቱ የተፈጸመበት ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, Image copyrightAFP

ታትሟል

የአገር ውስጥ ሚኒስትር የሽብር ክስተት ነው ባሉትና በደቡብ ምሥራቅ ፈረንሳይ በተፈጸመ የስለት ጥቃት ሁለት ሰዎች ሲገደሉ አምስቱ ደግሞ ቆስሉ።

በስለት በተፈጸመው ጥቃት ከቆሰሉት አምስት ሰዎች መካከል ሁለቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል።

የዓይን እማኞች እንዳሉት ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ ወደ አንድ የትንባሆ መሸጫ ሱቅ በመግባት የሱቁን ባለቤትና ተጠቃሚዎችን በያዘው ስለት ወግቷቸዋል።

በዚህም ሳያበቃ በአቅራቢያ ወደሚገኝ የሥጋ መሸጫ መደብር በመግባት ተጨማሪ ሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተነግሯል።

የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኀን እንደዘገቡት ጥቃቱን ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረው የ33 ዓመቱ ሱዳናዊ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።

ግለሰቡ በተያዘበት ጊዜ "መተላለፊያ መንገድ ላይ ተንበርክኮ በአረብኛ ቋንቋ ፀሎት ሲያደርግ ነበር" ሲል የአገሪቱ አቃቤ ሕግ ገልጿል።

እየተዘገበ እንዳለው ከሆነ ስለግለሰቡ ከዚህ በፊት በአገሪቱ ፖሊስም ሆነ በደኅንንት መስሪያ ቤቱ የሚታወቅ ነገር የለም።

ግለሰቡ ለፈጸመው ጥቃት ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስካሁን ያልተወቀ ሲሆን፤ የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ክሪስቶፈር ካስታነር ጥቃቱ በተፈጸመበት ከተማ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት እንዳሉት "ግለሰቡ በዚህ ድርጊት የሽብር ተግባሩን ጀምሯል" ማለታቸው ተነግሯል።

ሚኒስትሩ ጨምረውም ጥቃት ፈጻሚው ይህንን ድርጊት የፈጸመው ብቻውን ይሁን ከሌሎች ጋር በማቀድ የማወቁ ሥራ በአገሪቱ የጸረ ሽብርተኝነት አቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት በኩል የሚጣራ ይሆናል።

አቃቤ ሕግ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራቸው እንደሚያመለክተው ጥቃት ፈጻሚው "የሕዝብ ደኅንንት ለማወክ በማስፈራራት ወይም ሽብር ለመፈጸምና ነፍስ ለማጥፋት ተነስቷል" ሲል አመልክቷል።

በተጨማሪም በግለሰቡ ቤት ላይ በተደረገ ፍተሻ "በእጅ የተጻፉና ሐይማኖታዊ ትርጉም ያላቸው ሰነዶች ተገኝተዋል።"

ፖሊስ ጥቃቱን ከፈጸመው ግለሰብ ጋር ይኖር የነበረ አንድ ሌላ ሰውን በቁጥጥር ስር ማዋሉም ተዘግቧል።

የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከጥቃቱ በኋላ እንደተናገሩት አገራቸው በኮሮናቫይረስ ምክንያት በከባድ ሁኔታ ላይ ባለችበት በዚህ ወቅት ይህ መፈጸሙ ሐዘናቸውን እንደሚያበረታው ገልጸዋል።

ጨምረውም ጥቃቱን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ እንደሚቀርቡ ቃል ገብተዋል።