በኮሮናቫይረስ ከተያዘ ሰው ጋር የተነካኩ ሰዎችን የሚያድነው መተግበሪያ

የሞባይል መተግበሪያው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ነገሩ ቀላል የስልክ መተግበሪያ (App) ነው። ታላቋ ብሪታኒያ ሥራ ላይ ልታውለው እያብሰለሰለች ያለ ፈጠራ ሲሆን እያጎለበተው ያለው ደግሞ በታላቁ የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የቢግ ዳታ ኢንስቲትዩት ከኦክስፎርድ የሕክምና ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር ነው።

መተግበሪያው ዋንኛ ሥራው በኮሮናቫይረስ የተያዘን ሰው አድኖ መያዝ አይደለም፤ ይልቅስ በኮሮናቫይረስ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች በደቂቃ ውስጥ ስምና አድራሻቸውን ለይቶ ማቅረብ ነው።

ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?

ጥሩ ጥያቄ ነው፤ ዜጎች በቅድሚያ መተግበሪያውን በስልካቸው ይጭኑታል። እነሱ ሲንቀሳቀሱ፣ ሲበሉና ሲጠጡ በገቡበት ገብቶ በጂፒኤስ ይከታተላቸዋል። የትም ይሂዱ የት።

መተግበሪያው የዜጎችን እንቅስቃሴ መዝግቦ ስለሚይዝ እንበልና አንድ ሰው የበሽታውን ምልክቶች ቢያሳይ በፍጥነት ምርመራ እንዲያደርግ ያበረታታዋል።

አይበለውና ያ ሰው ቫይረሱ ቢገኝበት መተግበሪያው በፍጥነት ያ ግለሰብ ባለፉት ቀናት ቀርቧቸውና አብሯቸው የነበሩ፤ የተጠጋጋቸውን ሰዎች ሳይቀር ማንነትና ምንነት፣ ቁጥርና አድራሻ፣ አሁን በዚች ቅጽበት የት እንዳሉ የሚያመለክት መረጃን ይዘረግፋል።

ይህ ብቻም ሳይሆን ከተጠቂው ባሻገር ንክኪ የነበራቸው ሰዎች ራሳቸው ከሌላ ሦስተኛ ወገን ጋር የነበራቸውን ንክኪ በዛፍ ቅርንጫፍ አይነት ይተነትናል።

ኮሮና
Banner

ይህ መተግበሪያ እውን ሲሆን ልክ እንደ ፖሊስ መርማሪ አንድን በሽተኛ ባለፉት ቀናት ከነማን ጋር ተገናኝቶ እንደነበረ፣ እነማንን ጨብጦና ስሞ እንደነበረ፣ የት የት ሄዶ እንደነበረ ሁሉ አስታውሶ ከማናዘዝ በቀላሉ በመተግበሪያው በደቂቃዎች ውስጥ ይህን ሁሉ መረጃ በተፍታታ ሁኔታ ለማግኘት ያስችላል።

ይህ መተግበሪያ ታዲያ መርዶውን የሚያረዳው ለተጠቂው መርማሪ ሐኪሞች ብቻ ሳይሆን ቫይረሱ የተገኘበትን ሰው ባለፉት ቀናት ላገኙት ሁሉ ነው። "ወንድማችሁ በሽታው ተገኝቶበታል፤ አሁኑኑ ተመርመሩ፤ ራሳችሁንም ለይታችሁ ቆዩ" እያለ አስቸኳይ መልዕክት ያስተላልፋል።

ይህ መተግበሪያ ቫይረሱን በፍጥነት በመዋጋት ረገድ መለኛና ሁነኛ ልዩነት ያመጣል ብለዋል የእንግሊዝን መንግሥት የሚያማክሩ ሳይንቲስቶች።

ምክንያቱም ሳምንታት ይፈጅ የነበረውን ከበሽተኛው ጋር የተነካኩ ሰዎችን የማደኑን ሥራ መተግበሪያው በደቂቃ ስለሚያጠናቅቅ ነው።

ሌላው ጥቅሙ ይላሉ ከመተግበሪያው ፈጣሪዎች አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ክሪስቶፎር "…አንድ በሽተኛ ሲገኝ እርሱ የተገናኛቸው ሰዎች በሙሉ በደቂቃ ውስጥ ቶሎ ራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል። ይህም የበሽታውን ስርጭት በእጥፍ ይቀንሰዋል።

የሚደንቀው መተግበሪያው ቫይረሱ የተገኘበት ሰው የቆየባቸውን ካፌዎች፣ የበላባቸውን ሬስቶራንቶች፣ የተሳፈረባቸውን ታክሲዎችና የጎበኛቸውን ቢሮዎች ጭምር እየተከታተለ እነዚህ ድርጅቶች አካባቢያቸውን በጸረ ቫይረስ ርጭት እንዲያጸዱ ወዲያውኑ ይመክራል ተብሏል።

ይህ መተግበሪያ ለጊዜው ተግባራዊ አልሆነም። በምርምርና ጥናት ወረቀት ላይ ግን ታትሟል። አጋዥነቱ ከታመነበት በአጭር ጊዜ ወደ ትግበራ ሊገባ ይችላል።

ምን ያህል ሰዎች ይህንን መተግበሪያ በመጠቀም የግል ምሥጢራቸውንና የግል ሕይወታቸውን ለማጋራት ፍቃደኛ ይሆናሉ? ሲሉ ገለልተኛ ታዛቢዎች ስኬታማነቱን ይጠራጠራሉ።

ፕሮፌሰር ክርስቶፎር ግን በዚህ አይስማሙም፤ "ለስንት የማይረባ ነገር አይደለም እንዴ በስልካችን የጫናቸው መተግበሪያዎች የት እንዳለንና ወዴት እንደምንሄድ የሚያሳብቁት? ይህ እኮ የሰዎችን ሕይወት የማዳን ጉዳይ ነው፤ ለተቀደሰ ዓላማ የሚውል ነው።"

ይህ መተግበሪያ በኮሮናቫይረስ ከተያዘ ሰው ጋር የተነካኩ ስፍራዎችን ለይቶ በካርታ ከማሳየቱም ባሻገር ግለሰቦችን በንክኪ ደረጃ ለይቶ በሰንጠረዥ ያስቀምጣል። አንደኛ ተጋላጭ የሚባሉትን ከሩቅ ንክኪዎች ጋር በደረጃ በአንድ ላይ አይመድባቸውም።

ችግር የሚሆነው ካፌዎችና ሬስቶራንቶች ወይም አንዳንድ ቢሮዎች ዜጎች መተግበሪያቸውን ከፍተው ተጋላጭ እንዳልነበሩ እንዲያረጋግጡ ሲያስገድዱና ይህን ለማያደርጉት ደግሞ አገልግሎታቸውን ሲከለክሉ ነው።

ይህ ከሆነ መተግበሪያው ከጥቅሙ ጉዳቱ ያይላል፤ ሰዎችም አድልዎና መገለል ሊደርስባቸው ይችላል የሚል ስጋት አለ። ይህም ቢሆን ግን ምን ክፋት አለው? ይላሉ ሳይንቲስቶቹ። አላማችን የቫይረሱን ግስጋሴ መግታት አይደለም? በማለት።