ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የብሪታኒያ አየር ትራንስፖርት አደጋ ላይ መሆኑ እየተነገረ ነው
የብሪታኒያ አየር መንገድ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሚደርስበትን ኪሳራ የሚያካክስ በቢሊዮን የሚቆጠር ፓውንድ እንዲሰጠው የእንግሊዝ መንግሥትን ጠይቋል።
የአሜሪካ የጉዞ እገዳ አጠቃላይ የአትላንቲክ ውቅያኖስን የሚያቋርጠውን በረራውን ከማክሰኞ ጀምሮ ዝግ የሚያደርግ በመሆኑ በአየር መንገዱ ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ ሊሆን ይችላል ተብሏል።
በእርግጥ የታላቋ ብሪታኒያ መንግሥት አየር መንገዱን ጨምሮ በርካታ የቢዝነስ ተቋማትን ለመደጎም በጎ ምላሹን አሳይቷል።
አየር መንገዱ ግን የውሸት ሽንገላ አልፈልግም አፋጣኝ እርምጃ ያስፈልገኛል በማለት ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፏል።
"እያልን ያለነው ስለብሪታኒያ አየር መንገድ የወደፊት እጣ ፈንታ ነው፤ በዓለም አንዱ ተወዳዳሪ ስለሆነው የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ። መንግሥት የመፍትሔው አካል ካልሆነ በስተቀር ከዚህ ችግር ከወጣን በኋላ [ኮሮናቫይረስ] የዚህ አየር መንገድ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አይቻልም" ብሏል የአየር መንገዱ መልዕክት።
የአየር መንገዱ የእርዳታ ጥሪ የተላለፈው አሜሪካ የአውሮፓ የጉዞ እገዳዋን በማስፋት እገዳው ብሪታኒያንና አየርላንድንም እንደሚያካትት መግለጿን ተከትሎ ነው።
እገዳው ቀጣይ ማክሰኞ የሚጀምር ሲሆን ወሳኝ የሚባሉትን የጉዞ መስመሮችን የሚያካትት ሲሆን የብሪቲሽ አየር መንገድ፣ ቨርጂን አትላንቲክ እና የኖርዌይ አየር መንገድን ያካትታል።
አሜሪካ ከሰኞ ጀምሮ በርካታ የረጅም ርቀት ጉዞዎቿን እንደምትሰርዝ ይፋ አድርጋለች። ቅዳሜ እለት የውጭና የኮመን ዌልዝ ቢሮ ሁሉም ወደ ፖላንድ የሚደረጉ በረራዎች እንዲሰረዙና በጣም አስፈላጊ ካልሆነም ወደ ስፔን የሚደረግ ጉዞም እንዲቋረጥ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።
የእንግሊዝ መንግሥት በዚህ ውሳኔው የብሪቲሽ አየር መንገድ የሚገጥመውን ከፍተኛ ችግር እውቅና ሰጥቷል።
"ሠራተኞችን፣ የቢዝነስ ሰዎችንና ተጓዦችን ለመርዳት ከአየር መንገዱ አመራር ጋር እየሰራን ነው" ብሏል።
"የአውሮፓ ኮሚሽንን በማሳመን አየር መንገዶችን ጨምሮ ሁሉንም ቢዝነሶችና በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ወቅታዊ ችግር የገጠማቸው የግል ሠራተኞችንም ለመደጎም ዝግጅት እየተደረገ ነው" በማለት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠቱን ገልጿል።
በአውሮፓ ሕግ መሰረት በረራዎች የማይደረጉ ከሆነ ለአየር መንገዶች የተሰሩ የማኮብኮቢያና የማረፊያ መስመሮች ይነሳሉ። በዚህም ምንም እንኳ በቫይረሱ ምክንያት ተጓዦች ጉዟቸውን ቢያቋርጡም የተሰራለትን የማረፊያና የማኮብኮቢያ መስመር ላለማጣት ሲባል በባዶው ለመብረር መገደዱን ቨርጂን አትላንቲክ አስታውቋል።
የብሪቲሽ አየር መንገድም አርብ ዕለት ኢንዱስትሪው ከሳርስ በሽታ ወይም ከመስከረም 11ዱ [አሜሪካ ላይ የተፈጸመው የሽብር ጥቃት] በከፋ ሁኔታ ኪሳራ ላይ መሆኑን ለሠራተኞቹ አሳውቋል።
የብሪቲሽ አየር መንገድ ኃላፊ አሌክስ ክሩዝ እንዳሉት ከሆነ "ከመጥፋት የተረፈው ብሪቲሽ አየር መንገድ" የሚል ማስታወሻ ተለጥፎባቸው በርካታ አውሮፕላኖች የሚቆሙ ሲሆን በርካታ ሠራተኞችም ይበተናሉ።
ማክሰኞ ዕለት የኖርዌይ አየር መንገድ እንደገለጸው ከሆነ 4 ሺህ በራረዎችን ሰርዟል፤ ግማሽ የሚሆኑ ሰራተኞቹንም ለጊዜው አሰናብቷል።