ደቡብ አፍሪካ፡ "ማህፀኔን እንዳወጡት ለ11 ዓመት ያህል አላወቅኩም ነበር"

ቦንኪሌ ምሲቢ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያለፈቃዳቸው እንዲመክኑ ከተደረጉ 48 ሴቶች አንዷ ናት

የፎቶው ባለመብት, Bongekile Msibi

የምስሉ መግለጫ, ቦንኪሌ ምሲቢ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያለፈቃዳቸው እንዲመክኑ ከተደረጉ 48 ሴቶች አንዷ ናት
ታትሟል

ቦንኪሌ ምሲቢ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያለፈቃዳቸው እና ያለእውቅናቸው ዳግመኛ እንዳይወልዱ ከተደረጉ 48 ሴቶች አንዷ ናት።

በመንግሥት ሕክምና መስጫዎች ውስጥ 48 ሴቶች ሳያውቁና ፈቃድ ሳይሰጡ እንዲመክኑ መደረጋቸውን 'ኮሚሽን ፎር ጀንደር ኢኳሊቲ' ማስታወቁ ይታወሳል።

ቦንኪሌ በ17 ዓመቷ ልጅ ከወለደች በኋላ ያለፈቃዷ ዳግመኛ እንዳትወልድ መደረጓን ለቢቢሲ ተናግራለች። በወለደችበት ሆስፒታል ውስጥ ማህፀኗ እንዲወጣ መደረጓን ያወቀችው ልጇን በተገላገለች በአስራ አንድ ዓመቱ፣ ሁለተኛ ልጅ ለመውለድ ስትሞክር ነበር።

ቦንኪሌ በትውስታ 17 ዓመታት ወደኋላ ተመልሳ ታሪኳን ለቢቢሲ እንዲህ አካፍላለች

የመጀመሪያ ልጄን ወልጄ እንደተነሳሁ እምብርቴ አካባቢ በፋሻ ተጠቅልዬ ራሴን አገኘሁት። በወቅቱ ነገሩ ብዙም አላሳሰበኝም ነበር።

ልጄን የወለድኩት በቀዶ ሕክምና ነበር። በወለድኩኝ በአምስተኛ ቀኑ ከሆስፒታል ወጣሁ።

የወጣሁት ጤናማ ሴት ልጄን ይዤ ብቻ አይደለም። ሆዴ ላይ ትልቅ ጠባሳ ይዤ ጭምርም ነበር።

ያኔ ምን እንደተፈጠረ ያወቅኩት ከ11 ዓመት በኋላ ነበር።

ቦንኪሌ በ17 ዓመቷ

የፎቶው ባለመብት, Bongekile Msibi

የምስሉ መግለጫ, ቦንኪሌ በ17 ዓመቷ

ሁለተኛ ልጅ ለመውለድ ስሞክር ከ11 ዓመታት በፊት የተፈጠረው ተገለጸልኝ።

የመጀመሪያ ልጄን ከወለድኩ በኋላ ወሊድ መከላከያ እወስድ ስለነበር አለማርገዜ አላስገረመኝም።

ከእጮኛዬ ጋር ቀለበት ስናስር ሁለተኛ ልጅ ለመውለድ ስለወሰንኩ ወደ ሆስፒታል ሄድን።

ሀኪሙ መርምሮኝ ሲጨርስ፤ ተቀመጭ አለኝ፤ ከዛ ውሃ ሰጠኝና ማህፀን እንደሌለኝ ነገረኝ።

ከዛ በፊት ልጅ ወልጄ ስለነበር ሀኪሙ በነገረኝ ነገር ግራ ተጋባሁ።

ማህፀኔ ሊወጣ የሚችልበት ብቸኛ ቦታ የመጀመሪያ ልጄን የወለድኩበት ሆስፒታል እንደሆነ ተረዳሁ።

ያደረሱብኝ ነገር ይዘገንናል። ጨካኞች ናቸው።

የሆንኩትን ለመገናኛ ብዙሀን ተናገርኩ። ከዛም የጤና ጥበቃ ሚንስትሩ ልጄን የወለድኩበት ሆስፒታል ሄደው የወለድኩ ቀን እንደነበረ የተናገረውን ሀኪም አገኙት።

የቦንኪሌ ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Bongekile Msibi

የምስሉ መግለጫ, የቦንኪሌ የመጀመሪያ ልጅ

ሀኪሙ ይቅርታ አልጠየቀም። ያመከነኝ ሕይወቴን ለማዳን እንደሆነ ተናገረ። እውነቱን ለመናገር ከምን ሊያተርፈኝ እንደፈለገ አልገባኝም።

ሆስፒታሉ ውስጥ ምንም የሕክምና ማስረጃ የለም።

እንድመክን የተደረግኩት እኔ ብቻ አይደለሁም። ሌሎች 47 ሴቶችም የኔ እጣ እንደደረሳቸው የተደረገው ምርመራ ያሳያል።

አንዳንዶቹ ኤችአይቪ ስላለባቸው ማህፀናቸው መውጣቱ ተነግሯቸዋል። እኔ ግን ኤችአይቪ የለብኝም። እናም ለምን እንዲህ እንዳደረጉኝ አላውቅም።

ሀኪሙ ፈቃደኛነቴን የሚገልጽ ሰነድ እንደፈረምኩ ነግሮኛል። በፍጹም አልፈረምኩም። በወቅቱ ከ18 ዓመት በታች ስለነበርኩ ልፈርም አልችልም ነበር።

ሀኪሙ ኋላ ላይ የፈረመችው እናቴ አንደሆነች ተናገረ። እናቴ ግን ምንም ነገር አልፈረምኩም ብላለች።

የደረሰብኝን ነገር ከ11 ዓመት በኋላ ማወቄ ሕይወቴን እንዳልነበረ አድርጎታል።

አሁን ከእጮኛዬ ጋር ተለያይተናል። ልጆች መውለድ በጣም ይፈልግ ነበር። እኔ ግን መውለድ አልችልም። ስለዚህ የሚፈልገውን ነገር ከማሳጠው ብለየው ይሻላል።

ቦንኪሌ ሁለተኛ ልጅ መውለድ ትሻለች

የፎቶው ባለመብት, Bongekile Msibi

የምስሉ መግለጫ, ቦንኪሌ ሁለተኛ ልጅ መውለድ ትሻለች

እዛ ሆስፒታል የሚሠራውን ሀኪም ሳገኘው ምን እንደሻ ተጠየቅኩ። እኔ የምፈልገው ልጅ መውለድ ነው። በቅርቡ አንድ ነፍሰ ጡር የሥራ ባልደረባዬን ሳያት ስሜቴን መቆጣጠር ተሳነኝ።

ልጄ እህት ወይም ወንድም ትፈልጋለች። በጎዳና ተዳዳሪዎች በኩል ስናልፍ አንድ ልጅ ወስጄ እንዳሳድግ ትጎተጉተኛለች።

ሆስፒታሉ የኔን እንቁላል ተጠቅሞ ልጅ ለምታረግዝልኝ ሴት (ሰረጌት ማዘር) ገንዘብ መክፈል እንዳለበት አምናለሁ። ከሆነው ነገር ጀርባ ያለው አካል ተጠያቂ እንዲደረግም እፈልጋለሁ።

ሀኪሞቹ መብታችንን ገፈውን ሥራ እንዲቀጥሉ ልንፈቅድላቸው አይገባም። መቀጣት አለባቸው። የኛን ሕይወት ስላመሳቀሉት የእጃቸውን ማግኘት አለባቸው።

ዳግመኛ ልጅ እንዳይኖረኝ ያደረገው ሀኪም ይቅርታ እንዲጠይቀኝ እፈልጋለሁ።

አሁን ነገሩ እየታየ ያለውኮ የሰው ጣት እንደቆረጡ ያህል ቀለል ተደርጎ ነው። እውነታው ግን መላ እኔነቴን፣ ሴትነቴን ሰርቀውኛል።

ሰቆቃው መቼም ቢሆን አይወጣልኝም። ሰውነቴ ላይ ያለው ጠባሳ ደግሞ ሀዘኑን ዘወትር ያስታውሰኛል።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ምን አለ?

'ኮሚሽን ፎር ጀንደር ኢኳሊቲ' ጉዳዩን ለማጣራት ቢሞክርም፤ የታካሚዎች ፋይል እንደጠፋና የሆስፒታሉ ሠራተኞች ቀና ትብብር እንዳላደረጉለት ተናግሯል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጉዳዩን ማጋለጣቸውን ተከትሎ ኮሚሽኑ መርማሪዎቹን ወደ 15 ሆስፒታሎች መላኩን ገልጿል።

የደቡብ አፍሪካ ጤና ጥበቃ ሚንስትር ዚዌሊ ምኬዚ ከኮሚሽኑ ጋር ለመወያየት ጥያቄ እንዳቀረቡ ከመናገር በዘለለ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።