በሆንዱራስ አደገኛ ቦዘኔዎች ፊልም በሚመስል ኦፕሬሽን መሪያቸውን አስመለጡ

አደገኛ ቦዘኔዎቹ መሪያቸውን ያስመለጡት ከዚህ ሕንጻ ነበር

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, አደገኛ ቦዘኔዎቹ መሪያቸውን ያስመለጡት ከዚህ ሕንጻ ነበር
ታትሟል

በሆንዱራስ ሁለት መንግሥት ነው ያለው ማለት ይቻላል። የአደገኛ ቦዘኔዎች ጉልበት ከመንግሥት የማይተናነስ ነው። በጠራራ ፀሐይ ፊልም በሚመስል ወታደራዊ ኦፕሬሽን ያካሄዱት አደገኛ ቦዘኔዎቹ እጅግ ነውጠኛ የሚባለውን መሪያቸውን ከፖሊስ እጅ ፈልቅቀው አስመልጠውታል።

አሌክሳንደር ሜንዶዛ ይባላል በሙሉ ስሙ። እንደ ሜክሲኳዊው ኤልቻፖ ቅጽል ስም አለው፤ ኤል ፖርኪ የሚባል።

በዕለቱ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ነበረው። ኢል ፕሮግሬሶ የሚሉት ፍርድ ቤት የደረሰውም እጅግ በታጠቁ ኃይሎች ታጅቦ ሲሆን የሕንጻው 2ኛ ፎቅ ላይ ፍርዱን እየሰማ ነበር።

ድንገት የዚህ ኤምኤስ-13 የሚባለው የአደገኛ ቦዘኔ አባላት እስካፍንጫቸው ታጥቀው ወደ ፍርድ ቤቱ ቅጥር ገቡ። አለባበሳቸው ሙሉ የወታደር የደንብ ልብስ ስለነበረ ነውጠኞች እንደሆኑ የጠረጠረ አልነበረም።

በደቂቃዎች ውስጥ የፍርድ ቤት ሕንጻውን አውድመውታል። በትርምሱ ውስጥ አራት ጠባቂ ወታደሮችን ገድለው መሪያቸው ሜንዶዛን በክብር ይዘውት ወጥተዋል።

የሆንዱራስ ፕሬዚዳንት ሁዋን ኦርላንዶ ሄርናንዴዝ ቦዘኔዎቹን የሚጠቁም "አሁኑኑ 80 ሺህ ዶላር መጥቶ ይቀበለኝ" ብለዋል።

የአንደኛው ሟች አደገኛ ቦዘኔ ሬሳ በዚች ቀይ ተሽከርካሪ ውስጥ ተጥሎ ተገኝቷል

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የአንደኛው ሟች አደገኛ ቦዘኔ ሬሳ በዚች ቀይ ተሽከርካሪ ውስጥ ተጥሎ ተገኝቷል

ፖሊስ እንዳለው ሐሙስ ከሰዓት ላይ የመጡት አደገኛ ቦዘኔዎቹ በቁጥር 20 ይሆናሉ። የታጠቁትም እጅግ ዘመናዊ መሣሪያ ነበር። ፍርድ ቤቱ የሚገኘው የሆንዱራስ ሁለተኛ ከተማ በሆነችው ሳን ፔድሮ ሱላ ሲሆን መሪው እንዳያመልጥ በሚል ከፍ ያለ ጥበቃም ሲካሄድ ነበር።

በሆንዱራስ ቲቪ የተላለፈና ከደህንነት ጥበቃ ካሜራ (ሲሲቲቪ) ተገኘ የተባለ አንድ ተንቀሳቃሽ ምሥል ቅጂ ማንዶዛ እጁ በሰንሰለት ታስሮና በከፍተኛ ጥበቃ ወደ ፍርድ ቤት ሲገባ ያሳያል።

በደቂቃዎች ውስጥ ተመሳሳይ የወታደር ልብስ በለበሱ ሰዎች የተክስ እሩምታ ተከፍቶ ሰውየው እጁ ከሰንሰለት ነጻ ሆኖ ዘና ባለ ሁኔታ ታጅቦ ሲያመልጥ ይታያል።

ይህ ተንቀሳቃሽ ምሥል በአደገኛ ቦዘኔዎችና በፖሊስ መካከል የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድም ያሳያል።

በሆንዱራስ ፖሊስም ሆነ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የአደገኛ ቦዘኔዎች ሰንሰለት ውስጥ አሉበት የሚሉ መረጃዎች በስፋት ይወጣሉ።

በሌላ ተንቀሳቃሽ ምሥል ደግሞ ነውጠኛው ማንዶዛና ጋሻጃግሬዎቹ እየተታኮሱ ከመኪና መኪና እየቀያየሩ ሲያመልጡ ያሳያል።

የደኅንነት ምክትል ሚኒስትሩ ሉዊስ ሱዋዞ ወሮበሎቹን የገቡበት ገብተን እንይዛቸዋለን ሲሉ ዝተዋል።

ሞገደኛው አደገኛ ቦዘኔ አሌክሳንደር ሜንዶዛ ይህ ነው

የፎቶው ባለመብት, HONDURAN POLICE

የምስሉ መግለጫ, ሞገደኛው አደገኛ ቦዘኔ አሌክሳንደር ሜንዶዛ ይህ ነው

የአገሪቱ መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት ከሆነ ወሮበሎቹ ያመለጡባቸው መኪናዎች የትም ተጥለው፣ የሟች አስክሬኖችም ተበታትነው በመንገድ ታይተዋል። ከቦዘኔዎቹ የአንዱ ሟች አስክሬንም በቀይ መኪና ተጋድሞ ታይቷል።

ማንዶዛ እጅግ ነውጠኛ ከሚባሉ የመካከለኛው አሜሪካ የአደገኛ ቦዘኔ ቡድን መሪዎች አንዱ ሲሆን በፈረንጆች 2015 በቁጥጥር ሥር ውሎ 20 ዓመት ተፈርዶበት ነበር። ከዚያ በኋላም የሕገወጥ ገንዘብ ዝውውርና ሌሎች ወንጀሎች ተመስቶበት ፍርድ ቤት ይመላለስ ነበር።

ኤም ኤስ-13 የሚባለው የአደገኛ ቦዘኔዎች አደረጃጀት የተፈጠረው በፈረንጆቹ በ1980ዎቹ በሎስአንጀለስ ሲሆን የመሰረቱትም ከድሀ ቤተሰብ የተገኙና የኤልሳቫዶርን የእርስ በርስ ጦርነት የሸሹ ስደተኞች ናቸው።

የእርስ በርሱ ጦርነት ሲያበቃ የዚህ ቡድን አባላት ብዙዎቹ ከእስር ቤት እየተለቀሙ ከአሜሪካ ወደየ አገራቸው በግድ እንዲመለሱ ተደርገዋል። የቡድኑ አባላት ታዲያ የዚያ ዘመኑን የቦዘኔነት የሕይወት ዘይቤ ከሎስ አንጀለስ ይዘው ወደየአገራቸው ተመልሰው በተጠናከረ ሁኔታ ወንጀል ውስጥ ተሰማርተው ቆይተዋል።

አሁን ሆንዱራስን ጨምሮ በሳልቫዶር፣ በጓቲማላና ሌሎች የመካከለኛው አሜሪካ አገራት መረቡን ዘርግቶ በከፍተኛ ጉልበትና ገንዘብ ያንቀሳቀሳል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከመካከለኛው አሜሪካ በብዙ ቁጥር ሆነው የሜክሲኮ ድንበርን ለማቋረጥና አሜሪካ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞች የመሰደዳቸው ዋንኛ ምክንያት አድርገው የሚያነሱትም የዚህ ቡድን አባላት የሚያደርሱባቸው መከራ ነው።

ይህ ኤም ኤስ-13 የአደገኛ ቦዘኔ አደረጃጀት ጎልብቶ መካከለኛው አሜሪካን በአያሌው ያምሳታል።